እስራኤል እና ሐማስ የመጀመሪያው ዙር ድርድር በግብጽ ሻርም ኤል-ሼክ ውስጥ ማካሄድ ጀመሩ።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጋዛ ያለው ግጭት እልባት ያገኝ ዘንድ ባቀረቡት የሰላም ዕቅድ ዙሪያ ላይ ነው እስራኤል እና ሐማስ ቀጥተኛ ያልሆኑ ንግግሮች በግብጽ ሻርም ኤል-ሼክ ማካሄድ የጀመሩት።
በተጀመረው ድርድር የእስረኞች እና የታጋቾች ልውውጥ ላይ ከስምምነት መድረስ እንዲሁም የእስራኤል ወታደራዊ ኃይሎች ከጋዛ የተወሰኑ አካባቢዎች በከፊል መውጣት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ በዋናነት ትኩረቱን ያደረገ መሆኑን የፍልስጤም እና የግብጽ ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ገልጸዋል ።
እየተካሄደ ያለው የትራምፕ የሰላም ስምምነት እቅድ የመጀመሪያ ዙር የድርድር ሂደት በአዎንታዊ ድባብ መቀጠሉን የግብፅ የመንግሥት ሚዲያዎች ዘግበዋል።
ሐማስ ቀደም ሲል በትራምፕ በቀረበው የሰላም ዕቅድ በከፊል መስማማቱን ቢገልጽም፣ እስራኤል እና አሜሪካ ቁልፍ ብለው በያዟቸው ትጥቅ መፍታትና ቡድኑ ወደፊት በጋዛ በሚኖረው ሚና በተመለከተ ግን አቋሙን በግልጽ አላሳየም ።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቅዳሜ ዕለት በሰጡት መግለጫ በመጪዎቹ ቀናት ውስጥ ታጋቾችን መለቀቅ የሚቻልበት ሁኔታን ማሳወቅ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ የጋዛ ጦርነትን ለማስቆም በሚደረገው ጥረት ውስጥ የተሳተፉ ሁሉ “በፍጥነት እንዲንቀሳቀሱ” አሳስበዋል። በተጨማሪም የሰላም ዕቅዱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ማለትም የታጋቾችን እና እስረኞች ልውውጥ በዚሁ ሳምንት ይጠናቀቃል ተብሎ እንደተነገራቸው ገልጸዋል።
ታጋቾችን የመልቀቅ እና የረጅም ጊዜ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ድርድሩ በከፍተኛ ደረጃ እየተፋጠነ መሆኑን የአሜሪካ እና የግብፅ ባለሥልጣናትም ፍንጭ ሰጥተዋል።
ዘገባው የቢቢሲ እና ቲ አርቲ ዎርልድ ነው
በ ሰላማዊት ወልደገሪማ












