6ኛው የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ መንግስት ሀገር ኢኮኖሚን ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መንግስት ለዓመታት ሲያጠና ቆይቶ ተግባራዊ ባደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲሁም በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሞች ኢኮኖሚው በማንሰራራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለዘመናት በመዋቅራዊ ተግዳሮቶች ተፅዕኖ ውስጥ ወድቆ በእዳ ጫና ውስጥ መቆየቱን፤ በዘላቂ የፋይናንስ መሰረት ላይ ያልተዋቀረና ሀገርን ለከፍተኛ ዕዳ የዳረገ መሆኑ እና የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ጫና ፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ከለውጡ ወዲህ ግን መንግስት እንዚህን የኢኮኖሚ መዛባቶችን የሚያርሙ ፈጣንና መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ መሻሻያ ማድረጉን በመጠቆም፣ የመንግስት ገቢ፣ የወጪ ንግድ፣ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ለማሳደግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
የልማት አቅጣጫ ትኩረትም ውስን ከሆኑ ዘርፎች ወደ ባለብዙ ዘርፍ የኢኮኖሚ መሰረቶች በመቀየር ላይ ይገኛል፡፡ መንግስት ኢኮኖሚውን ከዕዳ ጥገኝነት በማላቀቅ ወደ ኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማሸጋገር የሚያስችል ወሳኝ ምዕራፍ ከፍቷል ብለዋል፡፡
የኢኮኖሚ ለውጡ መሰረቶችም ያሉንን አቅሞች ማወቅ፣ በችግር ውስጥ ዕድልን ማየት፣ በፈጠራ፣ በፍጥነትና በትብብርና የተለያዩ አቅሞችን በማሰባሰብ እንዲሁም ዘላቂ ግቦችን በማሳከት ላይ ያተኮሩ መሆናቸው ጠቁመዋል፡፡ እነዚህ መሰረቶችም አጠቃላይ ሀገራዊ እድገትን ለማፋጠን አስችለዋል፡፡
በዚህም ከዕዳ ጫና በመላቀቅ በራስ አቅም ችግሮችን በመፍታት፤ ከአግላይ የኢኮኖሚ ስርዓት ወደ አሳታፊና ምቹ የኢኮኖሚ ምህዳር በመሸጋገር፤ ከዝናብ ጥገኝነት ወደ ራስ ቻይ አምራችነት በመብቃት፤ የማዕድን ጥሪታችንን ወደ ወሳኝ የሀብት ምንጭነት በመቀየር፤ የቱሪዝም ሀብታችንን ከመዳህ ጉዞ ወደ ጉልህ የእድገት አንቀሳቃሽነት በመቀየር የህዝባችንን አኗኗር የመለወጥ እና ዘላቂ ተጠቃሚነቱን ለማረጋጋጥ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ፕሬዝዳንቱ አብራርተዋል፡፡
በዚህ መሰረት የኢትጵያ ኢኮኖሚ በ2017 በጀት 8 ነጥብ 8 በመቶ እድገት አስመዝግቧል ብለዋል፡፡
በ – ሰላም ይልማ












