የሸካቾ ባህላዊ አስተዳደር ሥርዓት “ምክረቾ”ን ለፍትህና ለሰላም መጠናከር ያለውን ሚና በማጎልበት ለክልሉ ሕዝብ የጋራ ተጠቃሚነት መስራት ይገባል ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ተናገሩ።
የሸካቾ ዘመን መለወጫ “ማሽቃሬ ባሮ” በክልሉ ሸካ ዞን ጌጫ ከተማ በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች በተከበረበት ወቅት ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት “ማሽቃሬ ባሮ” ከዘመን መለወጫ በዓልነቱ ባለፈ በርካታ ጠቃሚ እሴቶች አሉት።
በተለይ የበዓሉ አንዱ ዕሴት የሆነው ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት በአካባቢው ፍትህና ሰላም እንዲሰፍን ከማስቻል ባለፈ በመደበኛ ፍትህ ሥርዓቱ ላይ ያለውን ጫና በማቃለል እያገዘ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህንን ዕሴት ለሰላም ግንባታ ስራና የክልሉን ሕዝቦች አብሮነትና በጋራ የማደግ ፍላጎት ማጠናከር በሚያስችል መልኩ አጎልብቶ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።
የሸካቾ ባህላዊ አስተዳደር “ምክረቾ” በ2017 ዓ.ም ከ7ሺህ 400 በላይ አቤቱታዎችን በመቀበል ከ5ሺህ 800 በላይ የሚሆኑትን በባህላዊ የፍትህ አሰጣጥ ሥርዓት መፈታታቸውን በበዓሉ ወቅት ተገልጿል።
በአንድራቻ ወረዳ ጌጫ ከተማ ላይ በተከበረው “የማሽቃሬ ባሮ” በዓል ላይ የፌዴራልና የክልል የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።












