ዊሊያም ሳሊባ በአርሰናል ኮንትራት ለመፈረም መስማማቱ ተዘገበ። ፈረንሳዊው የመሃል ተከላካይ በመድፈኞቹ ቤት ውሉን ሊያድስ መቃረቡን ዘ ሰን ዘግቧል።
ዊሊያም ሳሊባ በአርሰናል አሁን ላይ ያለው ውል የሚጠናቀቀ በአውሮፓውያኑ 2027 ሲሆን፤ ሪያል ማድሪድ በቀጣይ ክረምት ውሉ ሊጠናቀቅ ሲቃረብ የማስፈረም ፍላጎት አለው በሚል ሲዘገብ ቆይቷል።
አሁን ላይ ተጫዋቹ በሰሜን ለንደኑ ክለብ ለመቆየት መወሰኑን ተከትሎ በቀጣዮቹ ቀናት ውሉን ማደሱ ይፋ ይደረጋል ተብሏል። የ24 አመቱ ተከላካይ ባለፉት አመታት በአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ የመጀመሪያ አሰላለፍ ላይ የሚካተት ከቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች ዋነኛው መሆኑ ይታወቃል።
በያዝነው የውድድር አመት በአንፊልድ ከሊቨርፑል ጋር በተደረገ ጨዋታ የጉልበት ጉዳት አጋጥሞት በሁለት ጨዋታዎች ከአሰላለፍ ውጪ እንደነበር ይታወሳል። ሆኖም ባሳለፍነው እሁድ ከማንችስተር ሲቲ ጋር በተደረገ ጨዋታ አገግሞ መመለስ ችሏል።
በአውሮፓ በአስደናቂ ብቃታቸውን ከሚጠቀሱ ወጣት ተከላካዮች አንዱ የሆነውን ሳሊባ በቡድኑ ማቆየት መቻሉ ለአርሰናል በስኬት ተጠቅሶለታል።
በ-አልፈሪድ ነስሮ












