በ2018 የውድድር ዘመን የእግር ኳስ ውድድሮች ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ውይይት በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር አስተናጋጅነት በ2018 የውድድር አመት የእግርኳስ ውድድርን ወደ መዲናይቱ ለመመለስ፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን፣የሊግ አክሲዮን ማሕበር እና የክለብ አመራሮችን በተገኙበት እየተወያየ ይገኛል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፤ የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት ሙሉ በሙሉ በመጠናቀቁ የእግርኳስ ውድድሩን ወደ ከተማዋ መመለስ አስፈልጓል ያሉ ሲሆን፤ ከዚያ አስቀድሞ የ2018 ውድድር አመትን ስኬታማ ለማድረግ መወያየት ይኖርብናል ብለዋል።

“የስፖርት ሜዳዎች ከዘር ልዩነት በመፅዳት አንድነት የሚያላብስ መሆን ይገባዋል” ያሉት ሚኒስትሯ “የጭቅጭቅና የንትርክ መድረክ እንዳይሆን ባለድርሻ አካላት ሊሰሩ ይገባል” ብለዋል።
በውይይት መድረኩ የ2018 የውድድር አመት ስፖርታዊ ጨዋነትን የሚያስገነዝብ ጥናታዊ ፅሁፍ ያቀረቡት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሣያስ ጅራ፣ ከኮቪድ ወረድሽኝ በኋላ ውድድሮችን በተለይም የሀገሪቱን ከፍተኛ የሊግ ውድድር ወደ አዲስ አበባ ይመለሳል ብለዋል።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አያይዘውም” ሙሉ በሙሉ ስፖርታዊ ጨዋነትን ማረጋገጥ የሚቻል ባይሆንም፣አደጋ እንዳይጋብዝ መከላከል ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል።
ውድድሩን አዲስ አበባ ላይ መካሄዱ ለእግርኳሱ እድገት፣የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣የሚዲያ ሽፋን ከማግኘት አኳያ ጠቀሜታዎች አሉት ሲሉም ገልፀዋል። ውይይቱ አሁንም እንደቀጠለ ይገኛል።
በአልፈሪድ ነስሮ












