ሊቨርፑል ከኢብራሂም ኮናቴ እያደረገ የሚገኘው የኮንትራት ማደስ ውይይት ውጤት አልባ እየሆን መምጣቱ ተነገረ። የመርሲሳይዱ ክለብ ፈረንሳዊውን የመሃል ተከላካይ በክለቡ ለማቆየት እያደረገ የሚገኘው ጥረት ስምምነት ላይ መድረስ አለመቻሉ ተነግሯል።
ኢብራሂም ኮናቴ ከቀዮቹ ጋር ያለው ውል በሰኔ 2026 የሚጠናቀቅ ሲሆን፤ አዲስ ውል መፈረም ካልቻለ በጥር የዝውውር መስኮት ከእንግሊዝ ውጪ ከሆኑ ቡድኖች ጋር ቅድመ ኮንትራት መፈረም ያስችለዋል።
ተጫዋቹ በአንፊልድ እንዳይረጋጋ የሚያደርገው ሪያል ማድሪድ ነው እየተባለ ሲሆን፤ አሌክሳንደር አርኖልድን እንደወሰዱ ሁሉ ኮናቴንም በነጻ ለመውሰድ እየሰሩ ነው ተብሏል። የ26 አመቱ ተከላካይ ወኪሎች በተለያየ ዙር ከሊቨርፑል ባለስልጣናት ጋር ውይይት ቢያደርጉም እስካሁን መግባባት ላይ መድረስ ተስኗቸዋል።
ኢብራሂም ኮናቴ ከጉዳት ነጻ ሆኖ በሙሉ አካላዊ ዝግጁነት ላይ ሲገኝ አስደናቂ አገልግሎት እንደሚሰጥ በተከታታይ የውድድር አመት ማሳየት ችሏል። ወሳኙን ተጫዋች የማጣት አደጋ ውስጥ የገባው ሊቨርፑል የፊታችን እሁድ ከሜዳው ውጪ ተጉዞ ከበርንሌይ የሚጫወት ይሆናል።
በ-አልፈሪድ ነስሮ












