ኒውካስል ዩናይትድ ዮኣኔ ዊሳን ከብሬንትፎርድ ለማስፈረም ተስማማ። በክረምቱ የዝውውር መስኮት አዋዛጋቢ ተብለው ከሚጠቀሱት ዝውውሮች መካከል አንዱ የሆነው የዊሳ ዝውውር መቋጫውን አግኝቷል።
ኒውካስል ዩናይትድ ለዝውውሩ 55 ሚሊየን ፓውንድ ዩሚከፍል ይሆናል። ማግፓይሶቹ ግማሹን ገንዘብ በዚህኛው ክረምት ቀሪውን ደግሞ በቀጣዩ ዓመት የሚከፍሉ ይሆናል ተብሏል። የ 28 ዓመቱ ተጨዋቾች ወደ ፊት ከኒውካስል የሚለቅ ከሆነ ብሬንትፎርድ ከሽያጩ 28% ድርሻ የሚኖረው ይሆናል።
በፈረንጆቹ 2021 8.5 ሚሊየን ፓውንድ ወጪ ተደርጎበት ከሎሪዮ ለንደን የደረሰው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተወላጁ ዊሳ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን 19 የፕሪሚየር ሊግ ጎሎችን ማስቆጠሩ ይታወሳል።
በሌላ ዜና አሌክሲስ ሳንቼዝ ወደ ሴቪያ እንደሚያመራ ተረጋግጧል። የቀድሞ የአርሰናል እና የማንችስተር ዩናይትድ ሰባት ቁጥር ለባሽ በቀጣይ ማረፊያው የአንዳሉሲያው ክለብ ሆኗል። ቺሊያው ኮኮብ ዝውውሩን ያጠናቀቀው በነፃ ሲሆን ባርሴሎናን ከለቀቀ ከ 11 ዓመታት በኋላ በስፔን ላ ሊጋ ዳግም ሲጫወት የምንመለከተው ይሆናል።
ዶዲ ሉኬባኪዮ 30 ሚሊየን ዩሮ ወጥቶበት ወደ ቤነፊካ ማምራቱን ተከትሎ ነው ሴቪያ ሳንቼዝን ተተኪ አድርጎ ለማስፈረም የወሰነው። ሳንቼዝ ባርሴሎናን ከለቀቀ በኋላ ባለፉት 11 ዓመታት ለስድስት የተለያዩ ክለቦች መጫወት መቻሉ ይታወሳል።
በ-ዳንኤል መምሩ












