በ2017 በጀት ዓመት ለ3 ነጥብ 25 ሚሊዮን ተገልጋዮች የኦንላይን ንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት መሰጠቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።
“የኢትዮጵያን ይግዙ” የንግድ ሳምንት ኤክስፖ 2017 መገናኛ በሚገኘው የጥራት መንደር እየተካሄደ ሲሆን እስከ ነሐሴ 29 ቀን 2017 ዓም ድረስ ክፍት ሆኖ ይቆያል። በዛሬው ዕለትም ከኤስፖው ጎን ለጎን የሀገር ውስጥ ንግድ ላይ ትኩረት ያደረገ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ የንግድ ምህዳሩን ለሸማቾች እና ንግዱ ማህበረሰብ ምቹ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል። በዚህም የሸማች እና የንግድ ማህበረሰቡ እርካታ እያደገ መምጣቱን ጠቁመው በቀጣይ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አንስተዋል።
ለገበያ መሰረተ ልማት መስፋፋት ትኩረት መሰጠቱን የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ ገበያውን ለማረጋጋት ከፍ ያለ ፋይዳ ያላቸው በርካታ የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች ወደ ስራ እንዲገቡ መደረጉንም አመልክተዋል።
ሚኒስትሩ ፣ ከህግና ስርዓት ውጪ የሚንቀሳቀሱ ላይም የሚወሰደው እርምጃ መቀጠሉንም ጠቅሰዋል። ለአብነትም በ2017 በጀት ዓመት 110 ሺህ ህገ ወጥ ድርጊት የፈጸሙ አካላት ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል ።
የንግዱን ዘርፍ ምቹ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ መሰል የውይይት መድረኮች በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለይቶ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማመላከት የላቀ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በጥራት መንደር የተዘጋጀውን “የኢትዮጵያን ይግዙ” ሀገራዊ የንግድ ሳምንት ኤክስፖ ነሐሴ 24 ቀን 2017 ዓ.ም መርቀው መክፈታቸው ይታወቃል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።












