የጥበብ ስራዎች በጠንካራ ህግ እንዲመሩ የሚያስችል የተደራጀ የጥበባት ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ከነሀሴ 28 እሰከ 30 የሚቆይ “ጥበባት ለኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት” በሚል መሪ ሃሳብ የሚያካሂደውን ሁለተኛውን ሀገር አቀፍ የኪነ-ጥበብ ውድድር አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ በሁለተኛው ሀገር አቀፍ የኪነ-ጥበብ ውድድር 364 ባለተሰጥኦዎች ይሳተፋሉ፡፡ ውድድሩ የሚከናወነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ በሚመረቅበት ወቅት እንደመሆኑ የጥበብ ስራዎቹ ከግድቡ ጋር ተያያዥነት እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡
በብሄራዊ ቴአትር በሚካሄደው ውድድር የሙዚቃ፣ ውዝዋዜ፣ በባህላዊ አልባሳት የፋሽን ውድድር፣ የስዕልና መነባነብ ስራዎች እንደሚቀርቡም ጠቅሰዋል። ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ የጥበብ ባለሙያዎች የአካባቢያቸውን ባህል የሚያሳዩበትና ህብረ ብሄራዊነትን የሚያንፀባርቁ ስራዎችን እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል።
በውድድሩ መክፈቻ ከኢትዮጵያ ኩባ ወዳጅነት ፓርክ እስከ ብሄራዊ ቴአትር ባለው ጎዳና የተለያዩ ትርኢቶች የሚቀርቡ ሲሆን በብሄራዊ ቴአትር ለመጀመሪያ ጊዜ የተጓዥ ተውኔት ይቀርባል።
የፖሊሲ ሰነዱ ላይ ግብዓት የማሰባሰብ ስራዎችም እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው፤ በዘርፉ የተለያዩ ማህበራትን በማሰባሰብ የሚያደራጅ የጥበባት ካውንሰል ለማቋቋም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ‘ሆፕ ፎር ኢትዮጵያን ፒዩፕልስ ‘ ከተሰኘ የበጎ አድራጎት ማህበር ጋር አብሮ መስራት የሚያስችላቸውን ስምምንት አድርገዋል። ስምምነቱ በሙዚቃ፣ ውዝዋዜና በመሳሰሉት ዘርፎች በጋራ ለመስራት የሚያስችል መሆኑን ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ተናግረዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።













