በምስራቅ አፍጋኒስታን በሬክተር ስኬል 6 የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ተከስቷል። አደጋው በአፍጋኒስታን ምስራቃዊ ክፍል የፓኪስታን ድንበር አቅራቢያ መከሰቱ የተገለፀ ሲሆን 8 ኪሎሜትር ጥልቀት እንዳለውም ተነግሯል ።
በዚህ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ቢያንስ 20 ሰዎች ሲሞቱ፣ ከ100 በላይ የሚሆኑ ደግሞ መቁሰላቸውን የአከባቢው ባስልጣናት ገልጸዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል። የዩናይትድ ስቴትስ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ (USGS) እንደገለጸው የሟቾችና ተጎጂዎች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል አስታውቋል ።
የመሬት መንቀጥቀጡ ከተከሰተበት ስፍራ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኙት ካቡል እና የፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ ድረስ መሰማቱ ተነግሯል። እሁድ ምሽት በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በሆስፒታሎች የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑ ሲጠቆም፣ የነፍስ አድን ስራዎችም መቀጠላቸው ነው የተነገረው።
የታሊባን መንግስት ባለስልጣናት በተራራማ አካባቢዎች አየተደረገ ያለውን የነብስ አድን ስራው ላይ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዲረዱ ጥሪ አቅርበዋል።
የኩናር ግዛት ፖሊስ አዛዥ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ በአከባቢው በተከሰተው የጎርፍ እና የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ምክንያት በደረሰው የመሬት መንሸራተት ወደ አካባቢው የሚወስዱ መንገዶች በመዘጋታቸው የነብስ አድን ስራውን ከባድ አድርጎታል ብለዋል።
በዚህም የነስብ አድን ስራው በሄሊኮፕተር ብቻ አየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል። የታሊባን ባለስልጣናት የተጎዱ አካባቢዎችን ለመድረስ የሚያስችሉ ሄሊኮፕተሮች ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዲቀርብላቸውም እየጠየቁ ነው።
በ – ሰላማዊት ወልደገሪማ












