በምስራቅ አሊፖ በሚገኘው ታል ማኤዝ ወታደራዊ ማዘዣ ላይ ጥቃት ሊፈጽሙ የነበሩ የSDF “አሸባሪዎችን” ሙከራ አከሸፍኩ ሲል የሶሪያ መንግስት አስታወቀ፡፡
የ YPG/PKK “የሽብር ቡድን” አንድ ክንፍ እንደሆነ የሚነገረው SDF በሰሜን ሶሪያ በተለያዩ ወታደራዊ ማዘዣዎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እንደነበር የደማስቆ መንግስት ገልጿል፡፡ የሶሪያ ወታደሮች “የሽብር ቡድኖች” ባሏቸው ላይ ተኩስ በመክፍት እንደተከላከሏቸው የሀገሪቱ የመንግስት ሚዲያ የሆነው ሳና መረጃውን አጋርቷል፡፡
የ SDF ሀይሎች በአም ቲኔህ እና ደይር ሀፊር በተባለ የሶሪያ ገጠራማ ቦታ መሽገው የሚገኙ መሆናቸውን አንድ ስማቸው ያልተጠቀሰ ባለሰልጣን መናገራቸውንም የመረጃ ምንጩ አስነብቧል፡፡ ባለፈው መጋቢት የሶሪያ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት በሀገሪቱ ከሚገኙ የታጠቁ ሀይሎች ጋር ከስምምነት መድረሱን እና በመንግስት ተቋማት ውስጥ እንዲሳተፉ ማድረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ሶሪያን ከመከፋፈል ለማዳን በተደረገው በዚህ ስምምነት የደማስቆ ፖለቲካ የተረጋጋ ቢመስልም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች ለአህመድ አልሻራ መንግሰት ፈተና መሆናቸው እንደማይቀር ይነገራል፡፡
አናዶሉ ዘግቦታል
ቶማይ መኮንን












