ናሽናል ሚዲያ አክስዮን ማህበር እና ኢትዮ መልቲሚዲያ የተለያዩ የውድድር ፕሮግራሞችን በጋራ ለማዘጋጀት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

ዘመኑ የደረሰበትን የሚዲያ እና የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሚዘጋጀው የውድድር ፕሮግራም፣ የቴሌቪዥን ተመልካቹን በቴሌቪዥን መድረክ የሚያሰባስብ እና ቤተሰባዊነትን የሚያጎለብት እንደሆነ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡
የናሽናል ሚዲያ አክስዮን ማህበር የማርኬቲንግ እና ሽያጭ ኃላፊ መኮንን ስዩም ኤን ቢ ሲ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የቤተሰብ ቴሌቪዥን መሆኑን እና ሁሉንም የቤተሰብ አባላት ያማከሉ፣ ባህልና ወግን የጠበቁ ፕሮግራሞችን ለተመልካች ለማድረስ አልሞ የተነሳ ጣቢያ መሆኑን አስታውሰው፤ ከኢትዮ መልቲሚዲያ ጋር በጋራ የሚዘጋጀው እና ዘመኑ የደረሰበትን የሚዲያ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ተመልካቾችን የሚያሳትፈው ይህ የውድድር ፕሮግራም ሰፊ ተወዳጅነትን እና ተቀባይነትን እንደሚያተርፍ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮ መልቲ ሚዲያ ዋና ስራ አስፈጻሚ አማኑኤል አክሊሉ፣ “እንቆካሽ” በሚል ስያሜ የበለጸገውን መተግበሪ በመጠቀም የሚዘጋጁት የተለያዩ የውድድር ፕሮግራሞች የሀገርን ህግና ሥርዓት አክብረው የሚፈጸሙ እና የሀገራችን የቴሌቪዥን ተመልካች በዓለም አቀፍ ደረጃ ካሉ ፕሮግራሞች ጋር የሚያስተዋውቅ ነው ብለዋል፡፡

“እንቆካሽ” መተግበሪያን በመጠቀም የቴሌቪዥን ተመልካችን በቤተሰብ ደረጃ የሚያሳትፉ ፕሮግራሞች ከ2018 በአዲስ ዓመት ለአየር እንደሚበቁ በስምምነቱ ላይ ተገልጿል፡፡












