የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት የ2018 ዓ.ም የስደስተኛ ዙር አምስተኛ ዓመት መክፈቻ እያደረገ ያለው ዝግጅት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ሎሚ በዶ አሳሰቡ።
የ2018 በጀት ዓመት እንደ ሀገር ታላላቅ የስኬት ምዕራፎች የሚከፈቱበት ነው ያሉት የተከበሩ ወ/ሮ ሎሚ በዶ ጽህፈት ቤቱም የምክር ቤቱን የመክፈቻ ሥነ-ሥርአት ይህን ታሳቢ በማድረግ ከፍ ባለ መልኩ ለማከናወን ከወዲሁ መዘጋጀት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የተከበሩ ወ/ሮ ሎሚ በሪፎርም በመረጃ ተደራሽነት እና በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ እስካሁን አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመው፤ የተለያዩ አስተዳደራዊ ሥራዎችን በተሻለ መልኩ በመፈፀም፣ በቀጣይ ሥራዎችን በየሳምንቱ በመገምገም እና ሠራተኞችን በማነቃቃት ፕሮግራሞችን ከወዲሁ ማጠናቀቅ እንደሚገባም ነው ያመላከቱት።
የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚንስትር የተከበሩ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በበኩላቸው በሪፎርሙ መሠረት የተደራጀው የሥራ አመራር የተሻለ ብቃት፣ የሥራ ቁርጠኝነት ያለው እንዲሆን ጥንቃቄ የተሞላበት ድጋፍና ክትትል ሲደረግበት እንደነበር አስታውሰዋል።
አመራሩ በቀጣይ የሚሠራቸው ሥራዎች ቀልጣፋ፣ ጥራት ያላቸው፣ ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት እንዲሁም የተገልጋይ ቅሬታን በፍጥነት የሚፈቱ መሆን አለባቸው ብለዋል።
የፓርላማ ቴሌቪዥንን በተመለከት የእስካሁኑ ሒደት ጥሩ ሆኖ አንዳንድ ያላለቁ ጉዳዮች ካሉ ግን በሶስት ቀናት ውስጥ አመራሩ ተነጋግሮ አቅጣጫ በማስቀመጥ ወደ ተጨባጭ ሥራ እንደሚገባም አመላክተዋል።
መረጃው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው












