ቡሄ መሠረቱ ሃይማኖታዊ ቢሆንም እንደየአካባቢው መልከ-ብዙ መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ትውፊታዊ ክዋኔዎች አሉት።
በሃይማኖታዊ አስተምህሮው ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር (ታቦር ተራራ) ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱን መግለጡን በማሰብ በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን በዓሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ዘንድ በድምቀት ይከበራል፡፡ ይህ በዓል በምእመናኑ ዘንድ “ቡሄ” በመባል ይታወቃል፡፡
“ቡሄ” ማለት መላጣ ወይም ገላጣ ማለት ነው፡፡ በአገራችን ክረምቱ፣ ጭጋጉ፣ ደመናው ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታይበት በዚሁ በዓል አካባቢ ስለ ኾነ በዓሉ “ቡሄ” ተብሎ ይጠራል፡፡
“ቡሄ” ሲመጣ የክረምቱ ጨለማነት አልፎ ወደ ብርሃን የሚሆንበት፣ ወገግታ የሚታይበት፣ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚሸጋገርበት ወቅት በመኾኑ ከቡሄ በኋላ የጠነከረ ክረምት አይኖርም፡፡
‘’ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት፤ ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት’’ እንዲሉ፡፡
በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የቡሄ ዕለት ማታ ችቦ ይበራል፡፡ ይህም በደብረ ታቦር ለታየው ብርሃነ መለኮት ምሳሌ ነው፡፡ ሕፃናቱ ይህ በዓል ከመድረሱ ቀደም ብለው ጅራፍ ሲገምዱና ሲያጮኹ ይሰነብታሉ፡፡ እናቶችም ለዚህ በዓል የሚኾን ሙልሙል ዳቦ ያዘጋጃሉ፡፡ ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ ሕፃናት በየቤቱ እየዞሩ
‘’ቡሄ ና በሉ፤
ቡሄ በሉ፤
ቡሄ መጣ፤
ያ መላጣ፤ ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ’’ እያሉ ይጫወታሉ፡፡ በዚህ ጊዜ እናቶች ካዘጋጁት ሙልሙል እያነሡ ይሰጧቸዋል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን በገለጠበት ዕለት እረኞች ከብርሃኑ የተነሣ እየተገረሙና እየተደነቁ ወደ ቤት አልተመለሱም ነበር፡፡ የልጆቹን መዘግየት ያዩ ወላጆች ችቦ አብርተውና ሙልሙል ይዘው ፍለጋ ወጥተዋል፡፡ ቡሄ ለሚሉ ልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጠውና በበዓሉ ችቦ የሚበራውም ከዚህ ታሪክ በመነሣት ነው፡፡
የቡሄ ዕለት ለቤተሰብ፣ ለዘመድ አዝማድ፣ ለጎረቤት ሁሉ ሙልሙል ዳቦ ይሰጣል። በቆሎ ተማሪዎች ዘንድም ደብረ ታቦር የተማሪዎች በዓል ነው። ተማሪዎቹ ቀደም ብለው “ስለ ደብረ ታቦር” እያሉ እህል፣ ብቅል፣ ጌሾ… ይለምኑና ጠላ ጠምቀው፣ ዳቦውን ጋግረው፣ ቆሎ ቆልተው ለደብረ ታቦር ዕለት ሊያስቀድሱ የመጡትን ምዕመናን ሁሉ ይጋብዛሉ።
በ-ሔርሜላ ተመስገን
ምንጭ፡- ማኅበረ ቅዱሳን ቲቪ እና የኢትዮጵያ የ5ሺ ዓመት ታሪክ መፅሀፍ












