በተያዘው የ2017/18 ዓ.ም የመኸር ወቅት ሀምሳ ሺህ ሜትሪክ ቶን ምርት ወደ መጠባበቂያ ክምችት ለማስገባት ግብ መቀመጡን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ገለጹ።
የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ከተቀመጡ ግቦች መካከል የመጠባበቂያ ክምችት አቅምን ማሳደግ ዋነኛው ነው ብለዋል አምባሳደር ሽፈራው።
ኢትዮጵያ በሁሉም የግብርና ምርታማነት መስኮች የምታስመዘግበው እመርታም የሀገርን የአደጋ ጊዜ የመጠባበቂያ ክምችት አቅም በማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸዋል። የክልል መንግስታትም የመጠባበቂያ ክምችት አቅም በማሳደግ የዕለት ደራሽ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች የሚያቀርቡበት አሰራር ተዘርግቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የመጠባባቂያ እህል ክምችት የሰብል ምርታማነትን አቅምን ማሳደግ የሚያስችል የ3 ቢሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ እንደተላለፈላቸው አስታውቀዋል። አሁን ላይ ቅጽበታዊ አደጋዎችን ምላሽ መስጠት የሚያስችል የ500 ሺህ ሜትሪክ ቶን የመጠባበቂያ እህል ክምችት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በተያዘው የ2017/18 መኸር ወቅት በመጀመሪያ ዙር 50 ሺህ ሜትሪክ ቶን የሰብል ምርት ወደመጠባበቂያ ክምችት ለማስገባት ግብ ተቀምጦ እየተሰራ ነው ብለዋል። ኮሚሽኑ ለመጠባበቂያ ክምችት የሚውለውን እህል በዚህ መልኩ ማድረጉ ለገበያ መረጋጋት ጉልህ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።
ለዚህ ስራ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚመራ አስተባባሪ ኮሚቴ የተዋቀረለት ሲሆን የፋይናንስ እጥረት የሚያጋጥማቸውን ክልሎች ለመደገፍ ያግዛል ብለዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።












