የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል ጥምረት በፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂ የሶላር ሚኒግሪድና የሶላር ፓርክ ፕሮጀክት ግንባታ ማስጀመሪያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ የ400 ሜጋ ዋት ሶላር ፓርክ እና 700 ኪሎዋት ሚኒ-ግሪድ ፕሮጄክት ውጥኖች ጨምሮ ቁልፍ የትብብር ስምምነቶች ያካተተ ነው፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚነስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) ከአለም አቀፍ ሶላር አሊያንስ (ISA) እና አጋር ድርጅቶች ጋር በትብብር የሚሰራው ስራ የኢትዮጵያን የኢነርጂ ሽግግር እንደሚያፋጥን ብሎም ፈጠራን እንደሚያጎለብት እና ኢንቨስትመንቶችን እንደሚያበረታታ ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት፣ የኢነርጂ ተደራሽነትን ለማጎልበት እና ፈጠራ እና ዘላቂ የኃይል አማራጮችን በመጠቀም የኢኮኖሚ እድገትን ለማሳደግ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በፀሀይ ሀይል ለመጠቀም እና የገጠር ኤሌክትሪፊኬሽንን ለማሻሻል ያላትን የማይናወጥ ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመላክቷል፡፡
የትሪጀክቱ ማሳያ የሆነው በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ግቢ የተተከለው የ100 ኪሎ ዋት የሶላር ጣሪያ የመኪና ማቆሚያ ስራ መጀመሩ የታዳሽ ሀይል መፍትሄዎችን ከህዝብ መሠረተ ልማት ጋር በማዋሀድ ለግሉ ሴክተር እና ለማህበረሰቡ አርዓያ ለመሆን ቁርጠኝነትን ያሳያል ተብሏል።
በኢትዮጵያ በሶላር ኃይል የሚሰራ ፓምፕን ተደራሽ በማድረግ ግብርናን ለማዘመን እንዲሁም የካርበን ልቀትን ዜሮ ያደረገ ኃይል በማስፋፋት የአየር ብክለት ለመከላከልም እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በ-ማህሌት ግርማ












