የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በመርሃግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ተቋሙ ከመደበኛ ተግባሩ ባሻገር ማህበራዊ ኃላፊነቱ ለመወጣት የተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡

በዛሬው መርሃግብርም በቂርቆስ ክፍለከተማ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ አንድ ሺህ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ በ2017 ዓ.ም የክረምት በጎ አድራጎት ፕሮግራም የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብርና የደም ልገሳ ተግባራትን ማከናወኑንም አንስተዋል፡፡
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ምስክር ነጋሽ (ዶ/ር) በክፍለከተማው የበጎ አድራጎት ስራን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን በመጠቆም የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የትምህር ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉ የእዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመንግስት ሰው ተኮር የሆኑ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ስራ አስፈጻሚው የነገ ሀገር ተረካቢ ህጻናትን ላይ ትኩረት ያደረጉ ስራዎች መስራት ከፍተኛ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ከቅድመ አንደኛ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃዎች የሚሰሩ ስራዎች ዓለም አቀፍ እውቅና ጭምር የተሰጣቸው መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈጻሚ ምስክር ነጋሽ በቂርቆስ ክፍለከተማ በተያዘው ክረምት ከ230 በላይ የአቅመ ደካማ ቤቶች መታደሱንም ጠቁመዋል፡፡
በ-ሰላም ይልማ












