ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የግብርና ምርቶችን ጥራትና ደህንነት ለማስጠበቅ የተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ወደ ውጭ በሚላኩና ወደ ሀገር በሚገቡ የግብርና ምርቶች ላይ የጥራትና ደህንነት ቁጥጥር ያደርጋል። የቁጥጥር ስራው የግብርና ምርቶችና አገልግሎቶች ደረጃቸውን የጠበቁ፣ የተመዘገቡና ብቃት ያላቸው እንዲሆኑ የሚያስችል ነው።
ባለስልጣኑ የግብርና ምርቶች፣ ቴክኖሎጂዎች፣ ግብዓቶች እና አገልግሎቶች ላይ የተጠናከረ ቁጥጥር ሲያከናውን መቆየቱን አብራርተዋል። በዚህም በ2017 በጀት አመት ወደ ውጭ በተላኩ የግብርና ምርቶች ግብይት ላይ ከጥራት እና ከደህንነት አንፃር ችግሮች እንዳልገጠሙ ገልፀዋል።
በበጀት ዓመቱ 877 ሺህ 350 ቶን ዕፅዋት እና የዕፅዋት ውጤቶች፣ 21 ሺህ 200 ቶን ስጋና ተረፈ ምርት፣ 621 ሺህ የቁም እንስሳት፣ 270 ቶን ሰምና የማር ምርቶች የቁጥጥርና የክትትል ስራ ከተካሔደባቸው ምርቶች መካከል ናቸው ብለዋል።
የቁጥጥር ስራዎቹ በአለምአቀፍ ደረጃ የተቀመጡ መስፈርቶችን መሰረት በማድረግ መካሄዳቸው ለውጤት መገኘት መሰረት መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ባለስልጣኑ በእንስሳት እርባታ፣ በአበባ እና በዕፅዋት እርሻ ላይ የማዳበሪያና የኬሚካል አጠቃቀምን ጨምሮ የምርት ጥራትን እንደሚከታተልም አብራርተዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 1 ሚሊዮን ኩንታል በሚጠጋ ምርጥ ዘር ላይ የጥራት ቁጥጥር በማድረግ ለአርሶ አደሩ እንዲሰራጭ መደረጉን በመግለጽ የግብርና ምርቶች ላይ የሚካሔደው የቁጥጥር ስራ በዋናነት የተጠቃሚውን ፍላጎት ለማሟላት ያለመ መሆኑንም አብራርተዋል።
በሚሌ የተገነባው የእንስሳት ኳራንቲን /ማቆያ / አለምአቀፍ ተቀባይነት ማግኝቱን ተከትሎ በርካታ የቁም እንስሳትን ወደ ተለያዩ ሀገራት መላክ መቻሉንም አክለዋል። የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን በመላው ሀገሪቱ 45 ኳራንቲን እና 4 የምርት መመርመሪያ ማዕከላት እንዳሉት መረጃዎች ያሳያሉ ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡












