የ37 አመቱ ፖላንዳዊ የፊት መስመር ተጫዋች ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ በአውሮፓውያኑ 2012 ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ለመጓዝ ከጫፍ ደርሶ እንደነበር ጠቁሟል።
ሌቫንዶቭስኪ በአስተያየቱ “ማንቸስተር ዩናይትድን ለመቀላቀል ተስማምቼ ነበር። ዶርትሙንድ ግን እኔን ለመልቀቅ ፍቃደኛ አልነበረም፣ምክንያቱም ካቆዩኝ ከፍ ያለ ገንዘብ ሊያገኙብኝ እንደሚችሉ ያስቡ ነበር” ብሏል።
ከአመታት በኋላ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ አለመጓዙ ይቆጨው እንደሆን ሲጠየቅ “ፕሪምየር ሊግ ላይ አለመጫወት ሊያስቆጭ የሚችል ነገር ይሆናል፣ነገር ግን ወደ ኋላ መለስ ብዬ ስመለከት ለባየርን ሙኒክ፣ ዶርትሙንድ እና ባርሴሎና በመጫወቴ በእግር ኳስ ህይወቴ ደስተኛ ያደርገኛል” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
ፖላንዳዊው አክሎም “የሆነ ነገር አምልጦኛል የሚል እሳቤ የለኝም፤ ምክንያቱም እያንዳንዱ እርምጃዬ ስለፈለኩት የወሰንኩት ነው” በማለት ምላሹን ሰጥቷል።
በሊዮኔል ሜሲ ተበልጦ ስላጣው የ2021ዱ ባላንዶር ተጠይቆ “የእግርኳስ ህይወቴ ምርጡ ጊዜ ላይ ነበርኩኝ” ያለ ሲሆን አሸናፊ ያላደረገኝ ምን እንደሆነ እስካሁን ለኔ ግልፅ አይደለም” ሲል ብስጭቱን ገልጿል።












