የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ “ዩክሬን ዶንባስ ክልልን አሳልፎ ለመስጠት የሚቀርብን ዕቅድ” እንደማትቀበል አሳወቁ።
እንዲህ ዓይነት ሀሳቦች በተኩስ አቁም ስም የመተግበር አጋጣሚው እንደሌላቸው ዘለንስኪ አሳስበዋል። ዶንባስን አሳልፎ መስጠት ለወደፊቱም ቢሆን ጦርነት እንዲቀሰቀስ በር የመክፈት ያህል ይቆጠራል በሚልም አስገንዝበዋል ፕሬዚዳንቱ።
ዘለንስኪ ይህን ያሉት ዶናልድ ትራምፕና ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዓርብ በአላስካ እንደሚገናኙ በተገለጸበት እና ዋሽንግተን ለሞስኮ ግዛት አሳልፍ ልትሰጥ ትችላለች የሚል መረጃ በወጣበት ሰዓት ነው።
በሌላ በኩል የሩሲያ ሀይሎች በዶንባስ ግዛት ላይ አሁንም የጥቃት አድማሳቸውን እያሰፉ ወደ ፊት በመገስገስ ላይ እንደሆኑም ይፋ ተደርጓል። ዘለንስኪም የሩሲያ ጦር መገስገሱን ቀጥሎበታል በሚል አምነው፤ ነገር ግን በዚህ ተግባር ውስጥ እየተሳተፉ ያሉትን ሀይሎች በቅርቡ እናወድማቸዋለን ሲሉ ዝተዋል።
ፑቲን ከትራምፕ ጋር ከመገናኘታቸው በፊት ሩሲያ ወደ ፊት እየገሰገሰች እና ግዛት እያሰፋች መሆኑን እንዲሁም ዩክሬን እየተሸነፈች ነው የሚል ግንዛቤ የመፍጠር ሂደት ላይ እንደሆነችም ዘገባው ያትታል።
ዶንባስ ክልል ሉሃንስክንና ዶኔትስክን የሚያካልል ሲሆን አሁን ላይ የሩሲያ እና የዩክሬን ሀይሎች እየተፋለሙ ከሚገኙባቸው ግንባሮች መካከል ነው። በአሁኑ ሰዓት ሞስኮ ሁሉንም የሉሃንስክ እና 70 በመቶውን የዶኔትስክ ክፍል መቆጣጠር ችላለች።
ቢቢሲ እንደዘገበው
በ-ቢኒያም ካሴ












