የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን የወንዝ ዳርቻን ከብክለት ለመከላከል የወጣውን ደንብ በተላለፉ ከ56 ሺህ በላይ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ ርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ የደንብ ጥሰትን በመከላከል የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ሰራተኞች የእውቅናና የምስጋና መርሃግብር አካሄዷል። በደንብ ማስከበር ላስመዘገበው የላቀ ውጤትም በከተማ አስተዳደሩ እውቅና ተበርክቶለታል።
የተቋሙ ሀላፊ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ እንደገለጹት፤ በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት በመዲናዋ የሚገኙ የወንዝ ዳርቻዎችን ከብክለት የመከላከል ስራ ተሰርቷል።
በመዲናዋ ያሉ ወንዞችን ከብክለት ለመከላከል የወጣውን መመሪያ የጣሱ 53 ሺህ 183 ግለሰቦችና ሶስት ሺህ 774 ተቋማት ላይ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል። በተወሰደውም ርምጃ አራት ሚሊዮን ብር ለመንግስት ገቢ ተደርጓል ሲሉ ተናግረዋል።
የደንብ ጥሰትንና ህገወጥ እንቅስቃሴን የመከላከል ስራ እየተሰራ ነው፤ በተሰራውም ስራ የከተማዋ የደንብ ጥሰት በ69 ነጥብ 8 በመቶ ቀንሷል ሲሉ ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ በተሰራ ደንብ የማሰከበር ስራ የመሬት ወረራን፣ ህገወጥ ግንባታን፣ የወንዝ ብክለትን የመከላከል ስራ ተሰርቷል።
አዲስ አበባን ከደንብ ጥሰትና ህገወጥ እንቅስቃሴ የፀዳች ለማድረግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስራ እየተሰራ መሆኑን የዘገበው ኢፕድ ነው።












