ዩንቨርሲቲዎች ከምንም አይነት ተፅእኖ ወጥተው ነፃ ሃሳብ የሚንሸራሸርበት እውቀት እና እውነት የሚፈልጉ ዜጎች መገኛ መሆን ይገባቸዋል-የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
በትላንትናው እለት በጎንደር ዩንቨርሲቲ መካሄድ የጀመረው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የለውጥ ምክር ቤት ዓመታዊ ጉባዔ ተጠናቋል።
ሁለት ቀናት የቆየው ጉባኤው በትምህርት ስርዓቱ ላይ እየተደረገ ስላለው ለውጥ የጋራ መግባባት ላይ የተደረሰበት እንደሆነ በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔ ተናግረዋል።
የፕሮግራሙን መዝጊያ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የለውጥ ምክር ቤት ዓመታዊ ጉባዔ ትክክለኛ ለውጥ የሚመጣበት እንጂ የመገማገሚያ መድረክ ብቻ አለመሆኑን ገልፀዋል።
አጠቃላይ ራፎርሙ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን የተናገሩት ፕሮፌሰሩ በትምህርት ዘርፉ ላይ የሚደረገው ሪፎረም ለቀጣይ አገር ተረካቢ ትውልድ በመሆኑ ችግሮችን መቋቋም የሚችል ጠንካራ ትውልድን ለመፍጠር ሪፎርሙ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ዩንቨርሲቲዎች ችግርን የሚቋቋም ትውልድን ከመፍጠር አኳያ ትልቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው ገልፀው ነገር ግን በዚህ ደረጃ የተደራጁ ችግር ፈቺ ትውልድን የሚፈጥሩ ዩንቨርሲቲዎች የሉንም ብለዋል።
ለዚህም የተስተካከለ የትምህርት ስርዓት አለመኖሩን እንደ ምክንያት አንስተው ተቋማዊ ለውጥ ያስፈልጋል ብለዋል።
መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የመምህራን ብቃትን ለማሳደግ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት እንደሚገኝ የገለፁት የትምህርት ሚኒስቴሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ዩንቨርሲቲዎች መወዳደር ያለባቸው በትምህርት ጥራት ብሎም በሚያበረክቱት የጥናትና ምርመር ውጤት መሆን ይገባዋል ብለዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያመርቷቸው ዜጎች የአገር ሉዓላዊነትን በሁሉም ዘርፍ የሚያረጋግቱ ብቃት ያላቸው መሆን እንደሚገባቸው ገልፀው በትምሀርት ጥራት ላይ በንቃት እና በፍጥነት ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነም ተናግረዋል።
ዩንቨርሲቲዎች ከምንም አይነት ተፅእኖ ወጥተው ነፃ ሃሳብ የሚንሸራሸርበት እውቀት እና እውነት የሚፈልጉ ዜጎች መገኛ መሆን ይገባቸዋል ይህንንም ለማሳካት ብዙ ስራ ይጠይቃል ብለዋል።
ሄርሜላ ፍቃደ (ከጎንደር)












