የጀርመኑ ክለብ ባየር ሙኒክ የሊቨርፑሉን የክንፍ ተጫዋች ልዊስ ዲያዝን ማስፈርሙን ይፋ አድርጓል። ባየርን ኮሎምቢያዊውን ተጫዋች የግሉ ለማድረግ 75 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ ማድረግ ችሏል።
በክለቦች አለም ዋንጫ ተሳታፊ የነበረው የአሰልጣኝ ቪንሰንት ካምፓኒ ቡድን በውድድሩ ላይ ወሳኝ ተጫዋቹን ጀማል ሙሲያላን በጉዳት ማጣቱ ይታወሳል።በተጨማሪም በስፍራው ላይ ሊጫወት የሚችለው የክለቡ ታሪካዊ ተጫዋች ቶማስ ሙለር ወደ ካናዳ ማቅናቱ አይዘነጋም።
ይህንን ተከትሎ የማጥቃት ስፍራ ተጫዋች የማስፈረም ግዴታ ውስጥ የገባው ባየርን ሙኒክ 29 አመት ሊሞላው ለተቃረበ ተጫዋች የተጋነነ የዝውውር ሂሳብ መክፈሉ አነጋጋሪ ሆኗል።
ዲያዝ በተጠናቀቀው የውድድር አመት አስደናቂ አቋም ካሳዩ የሊቨርፑል ተጫዋቾች አንዱ እንደነበር አይዘነጋም። ከዚህ ቀደም በነበሩ የውድድር አመቶች ተጫዋቹ የሚታወቀው ወጥነት ያለው አቋም ባለማሳየት መሆኑ ዝውውሩ ኪሳራ እንዳያመጣ አስጊ ያደርገዋል።
ባየርን ሙኒክ ከሁለት አመት በፊት በተመሳሳይ ዕድሜ የሚገኘውን እና በተመሳሳይ ስፍራ የሚጫወተውን ሳዲዮ ማኔን ከሊቨርፑል አስፈርሞ ዝውውሩ ሳይሳካ መቀረቱ አይዘነጋም።
በ-አልፈሪድ ነስሮ












