ኢትዮጵያ በትምህርት ቤት ምገባ በተሞክሮነት የሚወሰድ ውጤት ማስመዝገቧን የሮክፌለር ፋውንዴሽን የምግብ መርሃ-ግብር ዳይሬክተር ቤቲ ኪባራ ገለፁ።
የፋውንዴሽኑ የምግብ መርሃ ግብር ዳይሬክተርና የአፍሪካ ትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር አስተባባሪ ቤቲ ኪባራ እንዳሉት ፋውንዴሽኑ በአፍሪካ የትምህርት ቤት ምገባን እየደገፈ ይገኛል። ኢትዮጵያ በትምህርት ቤት ምገባ ተሞክሮ የሚሆን ተግባር እያከናወነች መሆኑን ጠቅሰው፤ ሀገሪቱ የአለም የትምህርት ቤት ምገባ ጥምረት አባል መሆኗንም አንስተዋል።
ፋውንዴሽኑ 100 ሚሊየን ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የ100 ሚሊየን ዶላር መርሃ ግብር የመተግበር እቅድ መያዙን ጠቁመው ኢትዮጵያም የዚህ እድል ተጠቃሚ ለመሆን ማመልከት እንደምትችል ገልፀዋል።
በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ 418 ሚሊየን ተማሪዎች በአፍሪካ ደግሞ 82 ሚሊየን ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል። የበለጠ ተማሪዎችን ለመድረስና ተጨማሪ 100 ሚሊየን ተማሪዎችን የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
አፍሪካ በራስ አቅም የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብርን ለማከናወንና ዘላቂ ለማድረግ የፋይናንስ አማራጮችን ማስፋት እንደሚጠበቅባትም ጠቁመዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡












