በቻይና ዋና ከተማ ቤጂንግ እና በአጎራባች ክልሎች በተከሰተው ከባድ ዝናብና ጎርፍ ከ30 በላይ ሰዎችን ህይወት መቀረጠፉን የሀገሪቱ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በአስር ሺ የሚቆጠሩ ነዋሪዎችም ከየቤታቸው ለመፈናቀል መገደዳቸው ነው የተነገረው ። ከቤጂንግ ከተማ ቅርብ ርቀት ላይ በሚገኙ ተራራማ አካባቢዎች በሚያን ወረዳ 28 ሰዎች ሲሞቱ፣ በያኒንግ ወረዳ ደግሞ 2 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።
በተመሳሳይ በሄቤይ ግዛት በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አራት ሰዎች ሲሞቱ መ፣ ስምንት ሰዎች ደግሞ እስካሁን አልተገኙም። ይህም በአጠቃላይ በአደጋው የሞቱት ሰዎች ቁጥር ቢያንስ 34 ያደርሰዋል ።
የነብስ አድን ስራው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ፣ በቤጂንግ እና በአጎራባች ግዛቶች በደረሰው ከባድ የጎርፍ አደጋ የጠፉ ሰዎችን ለማግኘት እና ለመታደግ “ሙሉ ትኩረት” እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።
ፕሬዝዳንት ሺ ባስተላለፉት መመሪያ “የጠፉ ወይም አደጋ ላይ ያሉ ሰዎችን ለመፈለግና ለመታደግ፣ የተጎዱ ነዋሪዎችን ለማዘዋወር እና ለማቋቋም እንዲሁም የሟቾችን ቁጥር በተቻለ መጠን ለመቀነስ ምንም ጥረት መተው የለበትም” ብለዋል።
ከባድ ዝናቡና ጎርፉ በቤጂንግ እና በአካባቢው የሚኖሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከመኖሪያቸው ያፈናቀለ ሲሆን በቤጂንግ ብቻ ከ80 ሺ በላይ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል ።
ከባድ ዝናቡ ሰፊ ጉዳት ያስከተለ ሲሆን በቤጂንግ 31 የመንገድ ክፍሎች ተጎድተዋል ፣ ከ130 በላይ መንደሮች የኤሌክትሪክ አቅርቦት ተቋርጧል። እንዲሁም በሌሎች ንብረቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል ።
በጎርፉ አደጋ በህይወት የተረፉ እና ህይወታቸው ያጡ ሰዎችን የማፈላለግ ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉም ተገልጿል ።
ዘገባው የቢቢሲ እና ዘ ጋርዲያን ነው
በ ሰላማዊት ወልደገሪማ












