በአሜሪካ ኒውዮርክ ሚድታውን ማንሃተን በሚገኘው ታዋቂ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ ውስጥ በተከፈተ የጅምላ ተኩስ ቢያንስ አምስት ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች መቁሰላቸው ተነግሯል ።
የብሔራዊ እግር ኳስ ሊግ (NFL) ዋና መስሪያ ቤትን ጨምሮ እንደ “ብላክስቶን” ያሉ ትላልቅ የፋይናንስ ተቋማትን በያዘው ህንጻ ውስጥ፣ አንድ ግለሰብ በሲቪሎች ላይ በከፈተው ጥቃት ነው በርካቶች ሰለባ የሆኑት ። ከተገደሉት አምስት ሰዎች መካከል አንድ ከስራ ውጪ የነበረ የኒውዮርክ ፖሊስ ዲፓርትመንት መኮንን እንደሚገኝበትም ተገልጿል ።
የኒው ዮርክ ከተማ የፖሊስ ዲፓርትመንት (NYPD) እንደገለጸው፣ ጥቃቱን የፈጸመው ሼን ዴቨን ታሙራ የተባለ የ27 ዓመት ወጣት መሆኑን አስታውቋል ። ግለሰቡ ጥቃቱን ሲፈጽም ኤ አር-15 (AR-15) ጠመንጃ ታጥቆ እና ጥይት የማያስተላልፍ ልብስ (bulletproof vest) ለብሶ እንደነበር የጸጥታ ምንጮች ገልጸዋል።
ግለሰቡም ጥቃቱን ካደረሰ በኃላ በህንጻው 33ኛ ፎቅ ላይ እራሱን በጥይት በመተኮስ ህይወቱ አልፏል። ይህ ድንገተኛ ጥቃት በከተማዋ ውስጥ ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሮ የነበረ ሲሆን፣ የጸጥታ ኃይሎች የህዝቡን ደህንነት ለማረጋገጥ የማጣራት ስራቸውን መቀጠላቸው ተዘግቧል ።
የፖሊስ እና የፌዴራል የምርመራ ቢሮ (FBI) ወኪሎች ጥቃቱ እንደተፈጸመ በፍጥነት ወደ ስፍራው በመድረስ ምርመራ እያደረጉም ይገኛል። የጥቃቱ መንስኤ እስካሁን ግልጽ ባይሆንም የፌዴራል የምርመራ ቢሮ እና የኒውዮርክ ፖሊስ የጋራ ምርመራ እያደረጉ ነው ተብሏል ።
የኒው ዮርክ ከተማ ከንቲባ ኤሪክ አዳምስ እና የፖሊስ ኮሚሽነር ጄሲካ ቲሽ በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ ሁኔታው መረጋጋቱን እና ጥቃቱን የፈጸመው ግለሰብ ብቻውን እንደነበር አረጋግጠዋል።
ታሙራ የቀድሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እግር ኳስ ተጫዋች እንደነበር የታወቀ ሲሆን፣ የብሔራዊ እግር ኳስ ሊግ (NFL) ዋና መስሪያ ቤት ለምን ኢላማ እንደተደረገ ወይም በጥቃቱ እና በተቋሙ መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት ስለመኖሩ ምንም የተረጋገጠ መረጃ የለም።
ዘገባው የሮይተርስ እና ኒውዮርክ ታይምስ ነው
በ ሰላማዊት ወልደገሪማ












