ሴንተር ፎር ሪስፖንሲብል ኤንድ ፒስፉን ፖለቲክስ ከሂራድ ፐብሊክ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ጋር በመቀናጀት ያዘጋጁት <<የመገናኛ ብዙሀን እና የጋዜጠኞቾ ሚና በግጭት መከላከል እና ሰላም ግንባታ በዲጂታል ዘመን>> በሚል መሪ ሀሳብ የምክክር መድረክ በሱማሌ ክልል ጅጅጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ መሀሙድ፣ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ፣ የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ፕሬዝዳንት ዛዲግ አብርሃ፣ ኬሪያ ኢብራሂምን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎች እየተሳተፉ ነው።
በተለያዩ አለመግባባቶች የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለማረጋጋትም ሆነ ለማባባስ ሚዲያ ያለው አቅም ከፍተኛ መሆኑን የሱማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ሙስጠፌ መሀሙድ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ከመገናኛ ብዙሀን ጋር ቆየት ያለ ትስስር አለው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በተለይም፤ ዓለም ዲጂታላይዝድ በሆነችበት በዚህ ዘመን ሚዲያው እና ህብተሰቡ ሀሰተኛ መረጃን በሚያሰራጩ በማህበራዊ ትስስር ገፆች እየተፈነተ ይገኛል ብለዋል።
መገናኛ ብዙሀንና ጋዜጠኞች እንደ ሀገር የሚስተዋሉ ግጭቶችን በመከላከል እና ሰላም በመገንባት ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉም ፕሬዝዳንት ሙሰጠፌ አሳስበዋል።
ላለፉት ዘመናት እንደ ሀገር የተፈጠሩ አወዛጋቢ ትርክቶች ዛሬ ላይ ትውልድ በተለያዩ ሀሳቦች እንዲከፋፈል ምክንያት መሆናቸውን በመድረኩ ተገልጿል። ከጠብመንጃ ይልቅ በማህበራዊ ሚዲያ የሚዋጉ ቡድኖች የሀገርን አንድነት ለመሸርሸር በሚያደርጉት ጥረት ወጣቶች የሀገራቸውን ሰላም እና አንድነት ለማስጠበቅ ዘብ መቆም እንዳለባቸው ተመላክቷል።
በዘጠኝ ክልሎች እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች የሀሳብ ማሰባሰብ ሂደት አያከናወነ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የኢትዮጵያ መፃኢን ብሩህ ለማድረግ ተስፋ ተጥሎበታል ነው የተባለው።
መገናኛ ብዙሀንን በመጠቀም የጋራ ትርክትን መገንባት ኢትዮጵያ ወደ ፊት ለምታደርገው ጉዞ ወሳኝ እርምጃ በመሆን የሀገርን አንድነት እንደሚያሰፍን በመድረኩ ተጠቁሟል።
በሀሴት ኃይሉ
ከጅጅጋ












