ከንቲባ ከድር ጁሃር ዛሬ በተጀመረው የአስተዳደሩ ምክር ቤት 3ኛ የሥራ ዘመን 4ኛ ዓመት 10ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የአስፈፃሚውንና የማዘጋጃ ቤት ተቋማትን የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበዋል።
ከንቲባ ከድር በሪፖርታቸው ላይ እንዳመለከቱት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሀገሪቱ የብልጽግና ጉዞን ስኬታማነት ለማረጋገጥ የሚያግዝ ህያው ፕሮጀክት ነው። ፕሮጀክቱ መንግስትና ህዝብ ከተቀናጁ የትኛውንም የልማት ፕሮጀክት ዳር ማድረስ እንደሚችሉ የተረጋገጠበት መሆኑንም አመልክተዋል።
ፕሮጀክቱ የዛሬው ትውልድ ለቀጣዩ ትውልድ ከፍታ የራሱን የልማት ጀግንነት ማህተም ያተመበት ታሪካዊ ክስተት ነው ሲሉም ጠቅሰዋል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለሕዳሴው ግድብ ከአስተዳደሩ ነዋሪ ከቦንድ ግዥ ከ5 ሚሊዮን 595 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ መደረጉንም አንስተዋል።
የቦንድ ሽያጩ በህዝባዊ ንቅናቄ ተጠናክሮ መቀጠሉን በመግለፅ፤ የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ዓመት ጀምሮ እስከአሁን ድረስ በቦንድ ሽያጭና በስጦታ ከአስተዳደሩ ከ108 ሚሊዮን 123ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል ሲሉም አስታውሰዋል።
በሌላ በኩል ከንቲባ ከድር ጁሃር ድሬዳዋ ከተለያዩ የዓለም ከተሞች ጋር የተፈራረመችው የእህትማማችነት ስምምነት ለሁለንተናዊ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎቿ እና ለማህበራዊ ልማቷ ወሳኝ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን አመላክተዋል።
በተጨማሪም በመላው ዓለም የሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆች እና ወዳጆች ለድሬዳዋ ዕድገት እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።
ለአብነትም በፈረንሳይ የሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች ከ95 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የህክምና ቁሶች ለአስተዳደሩ መደገፋቸውን ጠቅስዋል።
ዛሬ የተጀመረው የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት 3ኛ የሥራ ዘመን 4ኛ ዓመት 10ኛ መደበኛ ጉባዔ እስከ ነገ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ እንደሚመክር ታውቋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡












