ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ከጃፓን ጋር ግዙፍ የንግድ ስምምነት ላይ መድረሷን አስታወቁ ።
ፕሬዚዳንቱ በማህበራዊ ሚድያ ባሰፈሩት ጽሁፍ፣ ለወራት ከዘለቀው ከባድ ድርድር በኃላ አሜሪካ ትልቅ የንግድ አጋሯ ከሆነችው ጃፓን ጋር ግዙፍና ምናልባትም በታሪክ ትልቅ የንግድ ስምምነት መፈራረሟን ገልጸዋል ።
“አሁን በታሪክ ትልቁን የንግድ ስምምነት ፈርሜያለሁ፤ ምናልባት ከጃፓን ጋር በታሪክ ይሄ ትልቁ ስምምነት ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ” ሲሉ ትራምፕ ማክሰኞ አመሻሽ በዋይት ሀውስ ተናግረዋል ።
ስምምነቱ ለሁለቱም ወገኖች ትልቅ ጥቅም እንደሚያስገኝ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፣ ጃፓን በአሜሪካ 550 ቢሊዮን ዶላር ወይም 407 ቢሊዮን ፓውንድ ኢንቨስት እንደምታደርግ እና ወደ አሜሪካ ለምትልካቸው የጃፓን ምርቶች የ15 በመቶ የጋራ ታሪፍ እንደምትከፍል አስታውቀዋል።
ይህ ታሪፍ ከዚህ ቀደም ነሐሴ 1 ቀን ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ከታሰበው የ25 በመቶ የግብር ታክስ በእጅጉ የቀነሰ ነው። ትራምፕ ጃፓን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት ላይ በአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር ነሃሴ 1 ተግባራዊ የሚደረግ ታሪፍ እንደሚጥሉ መናገራቸው ይታወሳል ።
በአዲሱ የጃፓንና አሜሪካ የንግድ ስምምነት ጃፓን የመኪናዎች፣ ጭነት መኪናዎች፣ ለሩዝ እና የተወሰኑ የግብርና ምርቶች የኤክስፖርት ገበያዋን እንደምትከፍት ተጠቁሟል።
የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺጌሩ ኢሺባ፣ የድርድሩንና የስምምነቱን ዝርዝር በጥንቃቄ ከመረመሩ በኋላ እንጂ አሁን ላይ ስለ ውጤቱ ለመናገር እንደማይችሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ይሁን እንጂ፣ የጃፓን ዋና የንግድ ተደራዳሪ ራዮሴይ አካዛዋ ቀደም ሲል ዋይት ሀውስን ከጎበኙ በኋላ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ “ተልዕኮ ተሳክቷል” የሚል መልዕክት አስቀምጠዋል ።
ስምምነቱ መደረጉን ይፋ ከሆነ ወዲህ በገበያዎች ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል የተባለ ሲሆን፣ በቶኪዮ የጃፓን መመዘኛ የአክሲዮን ኢንዴክስ ኒኬይ 225 ወደ 2 በመቶ ከፍ ብሏል። በተለይም የመኪና አምራቾች ቶዮታ፣ ሆንዳ እና ኒሳን የአክስዮን ገበያቸው ማደጉ ተጠቁሟል።
ይህ ስምምነት ትራምፕ አስተዳደር ከፊሊፒንስ እና ኢንዶኔዢያ ጋር ካደረጋቸው ሌሎች የንግድ ስምምነቶች በኋላ የመጣ ነው። ፕሬዝዳንቱ በተጨማሪም ከአውሮፓ ህብረት ጋር የሚደረግ የንግድ ስምምነት ረቡዕ እንደሚታወጅ እና ተጨማሪ ስምምነቶች በቅርቡ እንደሚመጡ ፍንጭ ሰጥተዋል።
ዘገባው የቢቢሲ ነው
በ ሰላማዊት ወልደገሪማ












