የፍራንክፈርቱ አጥቂ ሁጎ ኤኪቲኬ ወደ ሊቨርፑል መጓዙን ተከትሎ ፊቱን ወደ ዮሃን ዊሳ ያዞረው ኒውካስትል ያቀረበው የዝውውር ጥያቄ ተቀባይነት አጥቷል።
ኒውካስትል ዩናይትድ ለኮንጎዋዊው አጥቂ 25 ሚሊዮን ፓውንድ ያቀረበ ሲሆን ብሬንትፎርድ ውድቅ አድርጎታል። ከሳምንታት በፊት በተመሳሳይ ተጫዋቾን ለማዘዋወር ኖቲንግሃም ፎረስት ጥያቄ ማቅረቡና ተቀባይነት ማጣቱ ይታወሳል።
ዮሃን ዊሳ በፖርቱጋል የቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅት በማድረግ ላይ በሚገኘው የብሬንትፎርድ የቡድን ስብስብ ውስጥ የተካተተ ሲሆን፣በክለቡ ስለሚኖረው ቆይታ ለመነጋገር ቀጠሮ እንደተሰጠው ዘ አትሌቲክ ዘግቧል።
የ28 አመቱ ዊሳ በግል ጥቅማ ጥቅም ዙሪያ ከኒውካስትል ጋር የተስማማ ሲሆን በያዝነው የዝውውር ገበያ ክለቡን መልቀቅ ይፈልጋል ተብሏል። ብርያን ምብዌሙን እና ክሪስቲያን ኖርጋርድን የመሳሰሉ ወሳኝ ተጫዋቾቹን ያጣው ብሬንትፎርድ ዊሳን የመልቀቅ ፍላጎት እንደሌለው ተነግሯል።
ተጫዋቹ የግድ መልቀቅ አለብኝ ካለም ብሬንትፎርድ ከ55 ሚሊዮን ፓውንድ በታች እንደማይቀበል ታውቋል።
በ-አልፈሪድ ነስሮ












