በኢትዮጵያ ለአንድ አመት ገደማ ተግባራዊ የተደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የተረጋጋና ሁሉን አቀፍ ዕድገት እንዲመዘገብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተገልጿል።
ይህም የተገለጸው እየተካሄደ ባለው የኢትዮጵያ ፋይናንስ ጉባኤ – የግል ዘርፍ መድረክ ላይ ነው።
በኢኮኖሚ ማሻሻያዉ የተወሰዱ በርከታ እርምጃዎች የዋጋ ግሽበት እና የእዳ ጫና እንዲቀንስ እንዱሁም የብድር እና የውጭ ምንዛሪ አገልግሎት እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆናቸው ነው የተነገረው።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ፣ የተሟላው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሀገሪቱን የዕድገት መጠን ማሳደጉን ገልጸዋል።
የውጭምንዛሪ ግኝት 8.3 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የገለጹ ሲሆን፣ በኤክስፖርት የተገኘው ውጤትም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ትክክለኛነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምሕረቱ በከፍተኛ ጥናትና ጥንቃቄ ተግባራዊ የተደረገው የተሟላው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ታሪካዊ ለውጥ የተመዘገበበት መሆኑን አስታውቀዋል።
በ2016 በጀት ዓመት ከሁሉም ምንጮች የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ 24 ነጥብ ሰባት ቢሊየን ዶላር እንደነበር በመግለጽ ከሪፎርሙ በኋላ የተገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ 32 ነጥብ አንድ ቢሊየን ዶላር መገኘቱን ተናግረዋል።
የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ መኖሩ ብቻ በቂ አይደለም የተባለ ሲሆን የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን ማሳደግ እንደሚገባ ተመላክቷል።
በጉባኤው የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱን ፣ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በ ያብስራ ብርሀኑ












