የእርዳታ ምግብ ለመቀበል ተሰልፈው የነበሩ 85 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጥቃት መገደላቸው ተነገረ።
በትላንትናው ዕለት እሁድ በጋዛ ሰርጥ ከእርዳታ ማዕከላት ምግብ ለመቀበል ተሰልፈው የነበሩ ቢያንስ 85 ፍልስጤማውያን በእስራኤል ጦር መገደላቸውን የአካባቢው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ግድያው ከሃያ አንድ ወራት በላይ በዘለቀው የእስራኤል- ሀማስ ጦርነት፣ የእርዳታ ምግብ በመጠባበቅ ላይ ሳሉ ከተገደሉ ፍልስጤማውያን በቁጥር ትልቁ እና አስከፊው ነው ተብሏል። ከዚህ በፊት ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር የተመዘገበው በሰሜናዊው ጋዛ ሲሆን፥ ቢያንስ 79 ፍልስጤማውያን በዚኪም መሻገሪያ በኩል እርዳታ ለማግኘት ሲሞክሩ የተገደሉበት ክስተት ነበር።
የተባበሩት መንግስታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም፥ ለተራቡ ዜጎች እርዳታ ለማድረስ ሲሞክሩ የነበሩ 25 የእርዳታ መኪኖቹ ላይ ጥቃት መድረሱን ጠቅሶ፥ ይህም እርዳታ ለማድረስ መስተጓጎል እንደፈጠረበት ገልጿል።
እስራኤል ከመጋቢት ወር ጀምሮ ፥ በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን እርዳታ እንዳይደርሳቸው ሙሉ እገዳ መጣሏ ይታወቃል። ለሁለት ወራት የቆየው የተኩስ አቁም መፍረሱን ተከትሎም በጋዛ የማያባራ ጥቃት እያካሄደች ትገኛለች።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተደጋጋሚ በጋዛ ረሃብ እያንዣበበ ነው የሚል ማስጠንቀቂያ ማሰማቱን ተከትሎ፥ እገዳው በከፊል ቢላላም አሁንም ፍልስጤማውያን በከፍተኛ የምግብ፣ የመድኃኒት እና የነዳጅ እጥረት በመፈተን ላይ ይገኛሉ።
በ- ሰላማዊት ወንድወሰን












