በቀጣዮቹ ቀናት የክረምቱ የዝናብ መጠን በብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየሰፋ እና እየጠነከረ ይሄዳል አለ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት፡፡
ኢንስቲትዩቱ እንደገለጸው፣ በተያዘው ሐምሌ ወር የክረምት ዝናብ በብዙ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ እየሰፋ እና እየጠነከረ የሚሄድ ሲሆን በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የተሻለ ዝናብ መጠንና ሥርጭት ይኖራል።
በዚህ መሰረትም በደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ሰሜን፣ መካከለኛው፣ ምስራቅ እና ሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ የዝናብ መጠንና ሥርጭት እንደሚኖር ተመላክቷል፡፡
እርጥበታማው የአየር ሁኔታ በተለይም በደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብና ሰሜን ምዕራብ የኢትዮጵያ አከባቢዎች ላይ በመጠንም ሆነ በሥርጭት እየተስፋፋ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያስተናግዳሉ ነ ያለው፡፡
በተጨማሪም በመካከለኛው፣ በሰሜን ምስራቅና በምስራቅ የሀገሪቱ አከባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ የሚኖራቸው ሲሆን፣ እንዲሁም በሰሜን ምስራቅ፣ መካከለኛው እና ምዕራብ የኢትዮጵያ አከባቢዎች ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ስለሚኖር አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል፡፡
የሚጠበቀው እርጥበት ለግብርና ሥራ እንቅሥቃሴ አዎንታዊ ሚና ቢኖረውም ስጋቶችን ለመቀነስና የሚኖሩትን መልካም አጋጣሚዎች ለመጠቀም የቀረቡትን ቦታ ተኮር የግብርና ሚቲዎሮሎጂ ምክረ ሀሳቦች በተገቢው ሁኔታ መተግበር ይገባል፡፡
ተቋሙ አክሎ፣ በአብዛኛው ተፋሰሶች ላይ ከመጠነኛ እስከ ከፍተኛ መጠን ያለው የገፀ ምድር የውሃ ፍሰት እንደሚኖራቸውና በተለይም ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ቅጽበታዊ ጎርፍ፣ የወንዞች ከፍታ መጨመር ሊያስከትል እንደሚችል አመላክቷል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ከሐምሌ 13 ጀምሮ ባሉ ተከታታይ 11 ቀናት በሁሉም የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት አከባቢዎች ይበልጥ እንደሚጠናከር ሲሆን፣ በደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ሰሜን እና መካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ ነጎድጓዳማ እና ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር ኢንስቲትዩት አስገንዝቧል፡፡












