የቀድሞው የ ናይጄሪያ ፕሬዝዳንት መሀመድ ቡሃሪ እ.ኤ.አ በታህሳስ 17 1942 በናይጄሪያ በዳውራ ግዛት ተወለዱ፡፡ ፕሬዝዳንት ቡሃሪ የአራት አመት ልጅ እያሉ አባታቸው መሞታቸውን ተከትሎ በእናታቸው እቅፍ አደጉ፡፡
የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዳውራ እና ማይዱዋ ግዛት ከ1948 እስከ 1952 ተከታትለዋል፡፡ ከ ካስቲናል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ1961 የሁለተኛ ደረጃ ሰርተፍኬት አገኙ። በዚሁ ዓመትም ወደ ናይጄሪያ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ኮሌጅ በመግባት የናይጄሪያ ጦርን ተቀላቀሉ።
እ.ኤ.አ. ከ1962 እስከ 1963 እንግሊዝ ውስጥ በሚገኘው የሞንስ ኦፊሰር ካዴት ትምህርት ቤት የመኮንኑ ካዴት ስልጠና ወስደዋል እንዲሁም በ 1963 ሁለተኛ ሌተናንት ሆነው ተሹመዋል፡፡
በመቀጠልም እ.ኤ.አ. በ 1965 በድጋሚ በእንግሊዝ በሚገኘው የጦር ሰራዊት ሜካኒካል ትራንስፖርት ትምህርት ቤት የሜካኒካል ትራንስፖርት መኮንኖች ኮርስ ተካፍለዋል።
ፕሬዝደንት ቡሃሪ በጣም የተከበሩ ባለስልጣን እንደመሆናቸው መጠን በወታደራዊ ስራቸው ወቅት በርካታ ቁልፍ ትዕዛዞችን እና የፖለቲካ ሹመቶችን ያዙ ነበር።
እ.ኤ.አ. በታህሳስ 1983 በተደረገው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ጄኔራል ሙሃመዱ ቡሃሪ የናይጄሪያ ጦር ሃይሎች ዋና አዛዥ ሆነው እስከ ነሐሴ 1985 ድረስ አገልግለዋል።
ጄኔራል ቡሃሪ በ1994 የፔትሮሊየም ትረስት ፈንድ (ፒቲኤፍ) ዋና ሊቀመንበር ሆነው ተሹመዋል።
በወቅቱ በጄኔራል ቡሃሪ የሚመራው ፒቲኤፍ በቀጥታ በስድስት ዋና ዋና ቦታዎች ላይ ስራወችን ሰርቶ ነበር፡፡ ከነዚህም መካከክል የመንገዶች ግንባታ እና ጥገና፣ የውሃ አቅርቦት፣ የትምህርት ቁሳቁሶች አቅርቦት እና የትምህርት መሠረተ ልማት ይጠቀሳሉ፡፡
በትልቅ የሀገር ፍቅር ስሜት እና ለብሄራዊ አገልግሎት ቁርጠኝነት በመመራት ጄኔራል ቡሃሪ በ1999 ናይጄሪያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መመለሷን ተከትሎ እ.ኤ.አ. በ2003 ወደ ፖለቲካ የገቡ ሲሆን የናይጄሪያ ህዝቦች ፓርቲ (ANPP) ተቀላቅለው በዚሁ ዓመት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን ተወዳድረው ነበር።
በ2003 በተደረገው ምርጫ ባይሳካላቸውም በተከታታይ ለሶስት ጊዜያት በመወዳደር እ.ኤ.አ. በማርች 28 2015 በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ህዝባዊ ድልን አጊንተው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡
ቡሃሪ በወታደራዊ አስተዳደር ናይጄሪያን የመሩ ሲሆን በኋላ ላይ በራሳቸው መንገድ ዴሞክራሲያዊ መንግስትን መስርተዋል፡፡ በ2015 ምርጫም በስልጣን ላይ የነበረን ፕሬዚዳንት በምርጫ በማሸነፍ ፖለቲካዊ ታሪክ የሰሩም ናቸው።
በሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ዙሪያ ስጋቶች እያደጉ ቢሄዱም ቡሃሪ በ2019 በድጋሚ ተመርጠዋል። ቡሃሪ ታጣቂ ቡድኖችን ለመዋጋት እና ኢኮኖሚውን ለማስተካከል የበለጠ ለመስራት ቃል የገቡ ቢሆንም በቀሪው የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ግን ያልተሳካ ጊዜያትን አሳልፈው ነበር፡፡
ቡሃሪ እ.ኤ.አ. በ 2022 ባደረጉት የመጨረሻ የተባበሩት መንግስታት ንግግራቸው የስልጣን ዘመናቸውን ሙጭጭ ብለው የሚያራዝሙትን መሪዎች ነቅፈው ነበር። በሚቀጥለው ዓመትም ከስልጣናቸው ወርደዋል፡፡ ቡሃሪ ቦኮ ሃራምን እና ሙስናን በመዋጋት ከፍተኛ ፖለቲካዊ ሚና እንደነበራቸው የሚነገር ቢሆንም የናይጄሪያ ህዝብ ግን ይህን ተግባር ሙሉ ለሙሉ አይቀበሉትም፡፡
ፕሬዝዳንት ቡሃሪ ሁለት ሚስቶች አግብተው፤ አስር ልጆችን አፍርተው ነበር፡፡ ብርቱው የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ቡሃሪ በእንግሊዝ የህክምና ክትትል ሲደረግላቸው ቆይቶ በ 82 ዓመታቸው ህይወታቸው አልፏል፡፡
በ ሔርሜላ ተመስገን












