በፋይናንስ ቀውስ ምክንያት ወደ ሊግ 2 እንዲወርድ ተፈርዶበት የነበረው ሊዮን በይግባኝ ዉሳኔውን ማስቀልበሱን ተከትሎ የፓላስ የቀጣይ ዓመት የኢሮፓ ሊግ ተሳትፎ ዕድል አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል።
በፈረንሳይ ሊግ 1 ስድስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ሊዮንና የእንግሊዝን ኤፍ ኤ ዋንጫ ያሸነፈው ክሪስታል ፓላስ ባለቤትነታቸው የአሜሪካዊው ቢሊየነር ጆን ቴክስተር ነው። ጆን ቴክስተር በቅርቡ የፓላስ ድርሻቸውን ሙሉ በሙሉ ለኒው ዮርክ ጀትስ ባለቤት ዉዲ ጆንሰን መሸጣቸውና ከሊዮን ሊቀመንበርነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸው አይዘነጋም።
ይሁን እንጅ የክሪስታል ፓላስ ድርሻቸውን የሸጡት ዩኤፋ ካስቀመጠው ቀነ ገደብ ከአውሮፓውያኑ መጋቢት 1 በኋላ መሆኑ ስምምነቱ እንዳይጸድቅ እንቅፋት ሆኗል። የኦሊቨር ግላስነር ቡድን ፓላስ የኤፍ ኤ ዋንጫውን ቢያነሳም በሊጉ ከሊዮን በታች አስራ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ እንደማጠናቀቁ የብዝሃ-ክለብ ባለቤትነት ህጉ ተግባራዊ ሲደረግ ተጎጅው የሚሆነው እሱ ነው።
የፊፋ የብዝሃ- ክለብ ባለቤትነት ህግ፣ በአንድ ባለሀብት ወይም ድርጅት ስር የሚተዳደሩ ክለቦች በተመሳሳይ መድረክ እንዲሳተፉ አይፈቅድም። በመሆኑም ለኮንፈረንስ ሊግ ተሳትፎ የሚያበቃውን ደረጃ ይዞ የጨረሰው ኖቲንግሃም ወደ ኢሮፓ ሊግ የሚገባበት ዕድል ሰፊ ነው ተብሏል።
በ-ይበልጣል ሰውነት












