እስራኤል በየመን ሁቲዎች የሚሳዔል ጥቃት ተሰነዘረባት፡፡
ከየመን የተወነጨፈውን ሚሳዔል የእስራኤል ጦር አክሽፊያለሁ ቢልም ስጋት የጋረጠ ጥቃት መሆኑ ግን ተነግሯል፡፡ የእስራኤል ጦር ሀይል(አይ ዲ ኤፍ) በቴል አቪቭ እና በሌሎች አካባቢዎች የአደጋ መቷል ድምጽ ሰጭ ደውሎች ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውንም አሳውቋል።
ዋና ከተማዋን ሰንዓን ጨምሮ ሰሜናዊ የመንን የተቆጣጠረው ሁቲ በእስራኤል ላይ ተደጋጋሚ የሚሳዔል ጥቃት ማድረሱን ቀጥሏል፡፡ እስራኤል ከቀናት በፊት በሆዴዳህ እንዲሁም አል-ኢሳ እና ሌሎች ስፍራዎች ላይ የአየር ጥቃት ማድረሷ የሚዘነጋ አይደለም።
ራሳቸውን አንስራላህ ብለው የሚጠሩት ሁቲዎች ከቀይ ባህር እስክ ኤደን ባህረ ሰላጤ እና አረቢያ ባህር ድረስ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸውን የንግድና ጦር መርከቦች ዒላማ ማድረግ ከጀመሩ ዓመት አልፏቸዋል።
ሁቲ ከፍልስጤሞች ጎን ነኝ በሚል የጀመረውን ዘመቻ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በተደጋጋሚ የገለጸ ሲሆን የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ካትዝ “እኛ ላይ እጁን ያነሳ እጁ ይቆረጣል “በሚል መዛታቸው ይታወሳል። ይህ ዜና እስከተጠናቀርውበት ሰዓት ሁቲዎች በጥቃቱ ዙሩያ ያሉት ነገር የለም።
ዘገባው የአልጀዚራ እና ታይምስ ኦፍ እስሬል ነው፡፡
በ-ቢኒያም ካሴ












