ቼልሲ ከፓልሜራስ ጋር በሚያደርገው የክለቦች የዓለም ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ የፔድሮ ኔቶን የመሰለፍ አለመሰለፍ ዉሳኔ ለእራሱ ለተጫዋቹ ትቶለታል።
ፖርቱጋላዊው አጥቂ በክለብና የብሔራዊ ቡድን አጋሩ እንዲሁም የቅርብ ጓደኛው ዲዮጎ ጆታ ድንገተኛ ህልፈት ሀዘን ላይ ይገኛል። ኔቶ የጓደኛውን ህልፈት ከሰማ በኋላ የትላንት ጠዋቱ የቼልሲ የልምምድ መርሐ ግብር ላይ አልነበረም።
ጆታ በ2020 በ41 ሚሊዮን ፓውንድ ሊቨርፑልን ከመቀላቀሉ በፊት ከኔቶ ጋር በዎልቭስ በአሰልጣኝ ኑኖ ኢስፕሪቶ ሳንቶ ስር አብረው ተጫውተዋል። ባለፈው ወር ስፔንን በመለያ ምት አሸንፎ የአውሮፓ ኔሽንስ ሊግ ዋንጫውን ያነሳው የሮቤርቶ ማርቲኔዝ ስብስብ አካልም ነበሩ።
የቼልሲ አሰልጣኝ ኤንዞ ማሬስካ “ፔድሮ በጣም አዝኗል፣ ምናልባት ከማዘንም በላይ፣ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ እሱን ለማጽናናት ከጎኑ ነን” ብለዋል። ነገ የመጫዎት አለመጫዎት ዉሳኔውን ሙሉ በሙሉ ለእርሱ እንደተውለት አክለው ተናግረዋል።
የቼልሲ ተከላካይ ማርክ ኩኩሬያም የአሰልጣኙን አስተያየት ያስተገባ ሲሆን ቡድኑ ኔቶን ለመደገፍ አንድ ላይ መቆሙን አስገንዝቧል።
በ – ይበልጣል ሰውነት












