የቀድሞ የካርዲፍ ሲቲ፣ አርሰናልና ዩቬንቱስ አማካይ አሮን ራምሴ የሜክሲኮውን ክለብ ፑማስን ተቀላቅሏል።
የ34 ዓመቱ ራምሴ ለሊጋ ኤምኤክሱ ተሳታፊ ፑማስ በይፋ ፊርማውን ማኖሩን ክለቡ ይፋ አድርጓል። ራምሴ ሜክሲኮ ሲቲ አየር መንገድ ሲደርስ “የዚህ ታሪካዊ ክለብ አካል በመሆኔ በጣም ደስተኛ ነኝ፣ ሜዳ ውስጥ እስክገባ ቸኩያለሁ” ብሏል።
ፑማስ ከአውሮፓውያኑ 2011 በኋላ አንድም የሊግ ዋንጫ ባያነሳም በሀገሪቱ ካሉ አራት እጅግ ዝነኛ ክለቦች መካከል አንዱ ነው። ይህ ዝውውር እንዲሳካ የአንበሳውን ድርሻ የተወጡት ከራምሴ ጋር በአንድ ወኪል ስር የሚገኙት የፑማስ አሰልጣኝ ኤፍራይን ሁዋሬዝ ናቸው ተብሏል።
ዌልሳዊው አማካይ በአርሰናል ቤት ቆይታው ሁለት ጊዜ የክለቡ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ሽልማትን አሸንፏል። ያለፈውን የውድድር ዓመት የልጅነት ክለቡ ካርዲፍ ሲቲን በጊዜያዊ አሰልጣኝነት እየመራ ነበር ያጠናቀቀው።
ሆኖም ግን ካርዲፍ ሲቲ ወደ ሊግ አንድ ከመውረድ አልተረፈም። ራምሴ ለዌልስ ብሔራዊ ቡድን 86 ጊዜ ተሰልፎ የተጫወተ ሲሆን ቡድኑ በዩሮ 2016 እስከ ግማሽ ፍጻሜው እንዲጓዝ ጉልህ አበርክቶት ነበረው።
በ – ይበልጣል ሰውነት












