በዘመናዊው እግር ኳስ አሁን ባለንበት ዘመን ለአንድ ክለብ ታምኖ መቆየት፣በክለብ ፍቅር የሚታወቅ ተጫዋች ማግኘት ቅንጦት እየሆነ መጥቷል።
እንደ ስቲቨን ጄራርድ እና ፍራንቺስኮ ቶቲ አይነት የአንድ ክለብ ስፖርተኞችን መመልከት ባይቻል እንኳን፣ለሚጫወቱበት ክለብ ከልብ የመነጨ ውዴታ እየተስተዋለ አይገኝም። የቀድሞው የመድፈኞቹ ቴክኒሽያን አማካኝ ስፔናዊው ሳንቲያጎ ካዞርላ፣በልጅነት ክለቡ ሪያል ኦቪዬዶ ያሳየው የክለብ ፍቅር በዚህ ዘመን ላሉ የስፖርቱ ቤተሰቦች ትንግርት ሆኗል።
ሳንቲ ካዞርላ በተሰጥኦ የታደለ፣በሁለቱም እግሩ በሚገባ መጫወት የሚችል፣እንኳንስ በሚጫወትለት ክለብ ቀርቶ በተቃራኒ በሚገጥመው ቡድን ደጋፊዎች ሳይቀር የሚወደድ ተጫዋች እንደነበር አይዘነጋም። ብዙዎች በሰሜን ለንደኑ አርሰናል የነበረውን ቆይታ ከህሊናቸው የማይጠፋ ሲሆን፣በተደጋጋሚ የሚገጥመው ዘግናኝ ጉዳት የተሰጥኦውን ያህል እንድይጓዝ አድርጎታል።
አሰልጣኝ አርሰን ቬንገር ከ22 አመት ቆይታ በኋላ ከመድፈኞቹ መለያየታቸው የኔንም የክለቡ ቆይታ አሰጥሮታል የሚለው ካዞርላ፣ተተኪው አሰልጣኝ ኡናይ ኢምሬ ተደጋጋሚ ጉዳት እየገጠመኝ በመሆኑ በቡድን ስብስቡ ቦታ እንደሌለኝ እና አዲስ ክለብ እንድፈልግ ነገረኝ ይላል።
ካዞርላ ወደ ቢጫ ሰርጓጆቹ ቪላሪያሎች ተመልሶ በመጓዝ ሁለት የውድድር አመት ካሳለፈ በኋላ ወደ ኳታር አቅንቶ በዣቪ ሄርናንዴዝ ወደ ሚሰለጥነው አል ሳድ ክለብ ተቀላቀለ። በኳታር በነበረው ቆይታ የነበረው ልምድ ለቡድኑ ውጤታማነት በእጅጉ ከማገዙም በላይ ተጫዋቹ በጉዳት ቢፈተንም ያለው እምቅ ችሎታ ፈጽሞ እንዳልካደው ማሳየት ችሏል።
በሩቅ ምስራቅ ያለው ውል ሲጠናቀቅ ሳንቲ እጅሜው 40 የደፈነ ጎልማሳ ቢሆንም፣አል ሳድ ተጨማሪ ኮንትራት ሊሰጠው ፍላጎት አሰይቶ ነበር። ስሙ የገዘፈ ኮከብ የማያመልጣቸው የሳዑዲ ክለቦችም ጠብደል ደመወዝ የሚያስገኝለት ጥያቄ ቢያቀርቡለትም የካዞርላ ፍላጎት በስፔን ሁለተኛ ዲቪዚዮን ወደሚጫወተው የልጅነት ክለቡ ሪያል ኦቪየዶ መጓዝ ሆነ።
በአውሮፓውያኑ 1984 የተወለደው ሳንቲያጎ ካዞርላ ጎንዛሌዝ የእግር ኳስ ህይወቱን የጀመረው ገና የ10 አመት ታዳጊ ሆኖ በሪያል ኦቪዬዶ አካዳሚ ነበር። ታዳጊው ካዞርላ እንደ አብዛኛዎቹ ላደጉበት ክለብ ፍቅር እንዳላቸው ተጫዋቾች በኦቪዬዶ አካዳሚ የመቆየት ፍላጎት ቢያሳይም፣ክለቡ በወቅቱ በገጠመው የፋይናንስ ቀውስ መነሻነት የትውልድ ከተማውን ክለብ ለቆ ወደ ማላጋ ከዚያም ወደ ቪላሪያል እንዲጓዝ አስገደደው።
ሳንቲ ከአስርት አመታት በኋላ ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፎ ወደ ኦቪዪዶ ሲመለስ ዳጎስ ያለ ደመወዝ አልፈልግም ብሎ በአመት 90 ሺ ዩሮ ብቻ እየተከፈለው ለመጫወት ሲስማማ ለክለቡ ካለው ፍቅር ነው። አስቀድሞ ለኦቪዬዶ በነጻ የመጫወት ፍላግቱን ቢገልጽም በስፔን እግርኳስ በነጻ መጫወት በህግ የተከለከለ በመሆኑ፣በሳምንት 1300 ዩሮ ብቻ እንዲከፈለው ሆኗል።
በስፔን የሊግ እርከን ሁለተኛ በሆነው በሴጉንዳ ቪዚዮን የሚጫወተው ሪያል ኦቪዬዶ በዘንድሮው አመት ወደ ላሊጋው ማደጋቸውን ካረጋገጡ ሶስቱ ክለቦች አንዱ ነው። ኦቪዬዶ ለመጨረሻ ጊዜ በስፔን ላሊጋ የነበረው በፈረንጆቹ ሚሊኒየም ሲሆን፣ከ25 አመታት፣ከሩብ ክፍለዘመን በኋላ ወደ ከፍተኛው ሊግ ሲያድግ የሳንቲ ካቮርላ ሚና የጎላ ነበር።
በሴጉንዳ ዲቪዚዮን በነበሩ የመጨረሻ ወሳኝ ሁለት ጨዋታዎች የካዞርላ ወሳኝ ግቦች ቡድኑ በሚገባ ጠቅመውታል፣የክለቡ ደጋፊዎች ሜዳውን በማጥለቅለቅ ደስታቸውን ሲገልጹ ቴክኒሽያኑ አማካኝ ስሜቱን መቆጣጠር ሲሳነው ታይቷል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም በሰጠው አስተያየት፣ ያ የሁለት ጊዜ የአውሮፓ ዋንጫው አሸናፊ፣በእንግሊዝ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ኤፍ ኤካፕን ድል ያደረገው አማካኝ፣በሕይወቴ የተሳተፍኩበት ምርጡ ጨዋታ ሲል ተናገረ።
የአንጋፋው ኮከብ የሪያል ኦቪዬዶ ቆይታን በተመለከተ እስካሁን የተባለ ነገር የለም። በብዙ ፈተናዎች አልፎም በቀጣይ አመት በአውሮፓ እግር ኳስ የምንመለከተው ይሆናል።
በ-አልፈሪድ ነስሮ












