በ2017 የውድድር ዘመን ከሊጉ የወረዱ ክለቦችም ባሉበት እንዲቆዩ ተወስኗል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በበርካታ አበይት ጉዳዮች ላይ ዉሳኔ አሳልፏል።
ኮሚቴው የሲዳማ ቡና ስፖርት ክለብ የሊጉን የፋይናንስ አስተዳደር መመሪያ በመጣሱ የቅጣት ዉሳኔ ቢተላለፍበትም በኢትዮጵያ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ የታገዱ ተጫዋቾችን አሰልፏል ብሏል። በመሆኑም ያሸነፈው የኢትዮጵያ ዋንጫ በፎርፌ ተሸናፊ ሆኖ ዋንጫው ለወላይታ ድቻ ተመላሽ እንዲደረግ ወስኗል። በውሳኔው መሰረት በ2018 ዓ/ም በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ውድድር ወላይታ ድቻ ኢትዮጵያን ወክሎ ይሳተፋል።
ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ፣ መቻል፣ ሀዋሳ፣ ሲዳማ እና መቐለ 70 እንደርታ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጸድቆ ስራ ላይ የዋለው የሊጉን የፋይናንስ አስተዳደር መመሪያ በመተላለፍ የተወሰነባቸውን የቅጣት ዉሳኔ ለፌዴሬሽኑ ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ይግባኝ ቢሉም ኮሚቴው ዉሳኔውን እንዳጸና አስታውሷል።
ይሁንና ከመቐለ 70 እንደርታ ውጪ 3ቱ ክለቦች ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና የፊፋ መተዳደሪያ ደንብ ዉጪ ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት በመውሰድና ውሳኔውን በማሳገድ እግድ የተጣለባቸው ተጫዋቾችን እንዲጫወቱ ማድረጋቸውን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ “ገምግሜያለሁ” ብሏል።
ክለቦች ከይግባኝ ሰሚ ኮሚቴው ዉሳኔ በኋላ በዓለም አቀፍ የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት ሊታይ ሲገባው ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት መውሰዳቸው የ3ኛ ወገን ጣልቃ ገብነትን አስከትሏል ሲል አክሏል። በመሆኑም 3ቱ ክለቦች የፍትህ አካላት ዉሳኔን በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲያደርጉና የተጣለባቸውን የገንዘብ ቅጣት በመክፈል ሪፖርት እንዲያደርጉ አሳስቧል።
መቐለ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፉ የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት መውሰዱ ይታወሳል። ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ክለቦች የታገዱ ተጫዋቾችን ያሰለፉባቸው ጨዋታዎች በሙሉ በፎርፌ ተሸናፊ እንዲሆኑም ወስኗል።
በ-ይበልጣል ሰውነት












