አሜሪካዊው ቢሊየነር በእንግሊዝ እግር ኳስ የሊግ እርከን ሁለተኛ ሆኖ ሻምፒዮንሺፕ የሚወዳደረውን ሼፍልድ ዌንስዴይን ለመግዛት ውይይት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።
የወቅቱ የክለቡ ባለቤት ጄፎን ቻንሲሪ ከወራት በፊት በሌሎች ባለሃብቶች ክለቡን ለመግዛት 48 ሚሊዮን ፓውንድ ቢቀርብላቸውም ውድቅ አድርገውታል።
ቴክስተር በተሻሻለ ዋጋ ክለቡን መግዛት እንደሚፈልጉ እና በእንግሊዝ እግር ኳስ ውስጥ መቆየት እንደሚፈልጉ እየተነገረ ይገኛል። ሼፍልድ ዌንስዴይ 24 ክለቦች በሚሳተፉበት በተጠናቀቀው ቻምፒዮንሺፕ 58 ነጥብ በመያዝ 12ኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል።
በቀጣይ ዓመታት ከረጅም ጊዜ ቆይታ በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊግ ይመለሳል የሚል ግምትም ተሰጥቶታል። አሜሪካዊው ባለሃብት ጆን ቴክስተር ከቀናት በፊት በክሪስታል ፓላስ ያላቸውን የ25 በመቶ ድርሻ መሸጣቸው ይታወሳል።
ፓላስ በቀጣይ አመት የይሮፓ ሊግ ተሳታፊ መሆኑ እና ባለሃብቱ በተመሳሳይ በይሮፓ ሊግ በሚሳተፈው በሊዮንም የባለቤትነት ድርሻ መያዛቸው፣በአንድ ባለቤት የተያዙ ሁለት ክለቦች በተመሳሳይ የአውሮፓ የውድድር መድረክ እንዳይሳተፉ የሚከለክለውን የዩኤፋ ሕግ የሚተላለፍ ሆኗል። ቴክስተር ፓላስ ከገባበት አጣብቂኝ እንዲወጣ በክለቡ ያላቸውን ድርሻ ለመሸጥ መገደዳቸው ይታወሳል።
በ-አልፈሪድ ነስሮ












