
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ያለውን የኢንዱስትሪ ክላስተር ዛሬ ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ ወቅት “የህዝባችንን ጥያቄዎች የምንመልሰዉ የሚታዩ፣ የሚጨበጡና ዘላቂ መፍትሄዎች ላይ በማተኮር ነዉ።” ብለዋል።
በ7 ቢሊዮን ብር ወጪ ግንባታው እየተከናወነ እና በ93 ሄክተር መሬት ላይ ያረፈው ይሄ የኢንዱስትሪ መንደር፣ የመጀመሪዉ ምዕራፍ ከ120 በላይ ሼዶች ያሉት ለብረታብረት ሥራ፣ ለእንጨት ውጤቶች፤ ለጨርቃ ጨርቅ ፣ ለፕላስቲክ እና ለኬሚካል ማምረቻነት፣ የምርት ማሳያ እና መሸጫ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ናቸዉ ተብሏል።
“ይህ ግዙፍ የኢንዱስትሪ መንደር የመስሪያ ቦታ ችግርን ከማቃለል ባሻገር የማኑፋክቸሪንግ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፍታት፣ ሰፊ የስራ ዕድልን ለመፍጠር የኢኮኖሚ ሽግግርን በማሳለጥ ረገድ ሚናው የላቀ ነው።” ያሉት ከንቲባ አያይዘውም፣ “የግንባታው ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ምርቶች የሚሆኑ ሼዶችን የያዘ ነው።” ብለዋል።
የኢንዱስትሪ መንደሩ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ሼዶች በተለየ ሁኔታ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን እና የኤሌክትሮ -ሜካኒካል ግብአቶችን መጠቀም ተችሏል ነው ያሉት።
ከኢንዱስትሪ መንደሩ በተጨማሪም ከቦሌ ኤርፖርት በጥቂት ደቂቃ መድረስ የሚያስችለውን አዲሱ የአቃቂ ቦሌ ካርጎ መንገድ አካባቢ መገኘቱ፣ ምርት ማጓጓዝን ታሳቢ ያደረገ እና ስትራቴጂክ ስፍራ ላይ የሚገኝ ፕሮጀክት ነው።












