ዛሬ በአማራ ክልል ደረጃ በጎንደር በተካሄደው የ3ኛው “የኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት” ንቅናቄ ኤክስፖ ላይ ተገኝተናል።
በከተማዋ የተገነባውንና በቀን 120 ቶን የአኩሪ አተር ዱቄትና በከፊል የተጣራ ዘይት የማምረት አቅም ያለውን የቲቲኬ ኢንደስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ፋብሪካንም መርቀናል።
ፋብሪካው እንደሃገር ለጀመርነው የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት እና የኤክስፖርትና ተኪ ምርት ፖሊሲያችን ውጤታማነት አንድ ሁነኛ አብነት ነው።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ክልላዊ የማጠቃለያ መርሐ ግብር በጎንደር ከተማ መካሄዱ ወደ ትናንትም፣ ወደ ዛሬም፣ ወደ ነገም ያሳየናል።
ጎንደር የአማራ ክልል በችግር ጊዜ ፀንቶ የመቀጠል ማሳያ በሚሆን መልኩ፤ በተሳሳተ መንገድ ወደጫካ ታጥቀው ገብተው የነበሩ ልጆቿ የያዝነው መንገድ አያዋጣም ብለው የመንግሥታችንን የሰላም ጥሪ ተቀብለው እየመጡ ወደማህበረሰባቸው እየተቀላቀሉ ይገኛሉ።

ጎንደር እንደ አዲስ እየተወለደች፣ እንደ አዲስ እየተሠራች፣ እንደ አዲስ እየፈካች ናት። ሕዝቡም የፅንፈኞችን መንገድ ታዝቦ ታዝቦ ነገሩ ገብቶታል፤ የበረሃ እርሻ እንጂ የበረሃ ሺፍታ አይፈልግም፡፡
መንግሥታችን ለሰላም እንዲሁም አምራች ኢንዱስትሪውን ጨምሮ ለልማት የሰጠውን ትኩረት አጠናክሮ ይቀጥላል።”- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ












