፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ የዘጠኝ ወራት የስራ አፈፃፀሙን እቅድ ከተቋሙ የስራ ሀላፊዎች፣ ከሌሎች ተቋማት ከተጋበዙ እንግዶች እና ከተቋሙ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ገምግሟል።
በግምገማ መድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት መንገሻ ፈንታው (ዶ/ር) ባለፉት ዘጠኝ ወራት የቢሯችን ዋና ዋና ተግባራት በእቅዱ መሰረት እንዲተገበሩ በርትተን ከመስራት በተጓዳኝ የክልሉ ህዝብ በአንፃራዊነት ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖር በርካታ ጥረት አድርገናል ብለዋል።

የክልላችን ህዝብ ወደ ቀደሞ ሰላሙ እንዲመለስ በዋነኛነት የመንግስት ሰራተኛውም ሆነ የክልሉ ነዋሪ ከተሰጠው ሙያዊ ሀላፊነት በተጨማሪ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ ያሳሰቡት ኃላፊው ለክልሉ ሰላም በዲጅታል ሚዲያው በኩል በተለይም ሀሰተኛ መረጃዎችን በማክሸፍ ረገድ ሰፊ ስራ ሰርተናል ያሉት ኃላፊው እነዚህን ሀገር አፍራሽና ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ መረጃዎችን በዲጂታል ሚዲያ ስራችን የመመከት ስራ መሰራት ችለናል ሲሉ ተናግረዋል።

በግምገማ መድረኩ የማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት የቢሮው ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሉነህ ዘበነ ሁላችንም በተደመረ ሀቅም ብዙ ጥረቶች አድርገናል፤ ብዙ ስኬቶችንም አስመዝግበናል ብለው ኮሙኒኬሽን ተቋሙ ውጤታማና ጥሩ ፈፃሚ እንዲሆን ከሌሎች ተቋማት በተሻለ ሪፎርም መደረግና መደገፍ እንዳለበትም አሳስበዋል ።

የቢሮው ም/ኃላፊ ወ/ሮ ትብለጥ መንገሻ በበኩላቸው በዚህ በአስቸጋሪ ሰዓት ጥሩ የአፈፃፀም ውጤት በመመዝገቡ የተቋሙን ሰራተኞች አመስግነው የስራ አፈፃፀሙ በርካታ መሻሻሎችና ለውጦች አሳይቷል ብለው አሁን ባለው ሁኔታ አንፃራዊ ሰላም በመምጣቱ ከዚህ የተሻለ መፈፀም እንደምንችል ሙሉ እምነት አለኝ ሲሉ ተደምጠዋል። ዘገባው የአማራ ኮሙኒኬሽን ነው፡፡












