የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በስህተት ከ200 ወንበዴዎች ጋር ቀላቅለው ወደ ኤል ሳልቫዶር አንድ አባት መመለሳቸው አነጋጋሪ ሆኗል።
የትራምፕ አስተዳደር ስህተቱን ቢያምንም ይህን አባት ከኤል ሳልቫዶር ወህኒ ቤት ማስወጣት እንደማይችል ተገልጿል፡፡
ወንበዴ የተባሉ ሰዎች ጋር ተቀላቅሎ ወደ ኤል ሳልቫዶር የተወሰደው ኪልማር አብሬጎ ጋርሺያ 29 ዓመቱ ሲሆን በአሜሪካ የመኖር ህጋዊ ከለላ የተሰጠው የሳልቫዶር ዜጋ ነበር።
ከኤል ሳልቫዶር የፈለሰውም በአገር ቤት ያለውን ግጭት በመሸሽ እንደነበር የሚያስታውሱት የህግ ባለሙያዎች በአስራዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ እያለ ነበር ወደ አሜሪካ የገባው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
ግለሰቡ በፈረንጆቹ 2019 በአሜሪካ የኢሚግሬሺን ዳኛ ከለላ እንዲያገኝ ተደርጎ እንደማንኛውም በህግ ዋስትና ስር እንደሚንቀሳቀስ ዜጋ በሜሪላንድ ኖሯል፡፡
በዚህ ወር (መጋቢት መጀመሪያዎቹ) አብሬጎ ጋርሺያ ከስራ በኋላ ልጁን ይዞ ወደ ቤቱ ሲሄድ በአሜሪካ የፍልሰት እና ጉምሩክ ኢንፎርስመንት (ICE) ኤጀንት እንዲቆም ታዞ” የህጋዊ ከለላ ሁኔታው” መለወጡ ይነገረዋል፡፡

ከሶስት ቀናት በኋላም መከረኛው አብሬጎ ጋርሺያ በማያውቀው ከ200 በላይ የሳልቫዶር እና ቬንዙዌላ ትራምፕ “ወሮበላ” ከሚሏቸው ሰዎች ጋር እጅና እግሩ ታስሮ ወደ አስፈሪው ኤል ሳልቫዶር ማጎሪያ ተወስዷል።
ፍርድ ቤት ግለሰቡ ያለአግባብ በስህተት ወደ ኤል ሳልቫዶር ተወስዷል ቢልም፣ የትራምፕ አስተሳደር አብሬጎ ጋርሺያን መመለስ እንደማይችል ተናግሯል፡፡
አይ ሲ ኢ (ICE) ወደ ኤል ሳልቫዶር እንደማይመለስ የህግ ከለላ እንዳለው ቢያውቅም በአስተዳደር ስህተት ምክንያት ወደ ኤል ሳልቫዶር ወህኒ ቤት ለዛውም ከወንበዴዎቹ ጋር ገብቷል ተብሏል፡፡
የአሜሪካ ዳኞች የፍትህ እጦት ሰለባውን ግለሰብ መመለስ እንደማይችሉ ያሳወቁ ሲሆን በስህተት ለተገፋው ግለሰብ የሚሆን ስርዓት በአሁኑ ሰዓት እንደሌለም ተናግረዋል፡፡
ዘገባው የሲ ኤን ኤን እና ዘ ዋሽንግተን ፖስት ነው፡፡
በ-ቢኒያም ካሴ












