።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
በመጋቢት 24 የመጣው ሁለንተናዊ ለውጥ በኢኮኖሚ፣በማህበራዊ፣በፖለቲካዊ እና በዲፕሎማሲ የተገኙ ውጤቶች የኢትዮጵያን ከፍታ የጨመረ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
ለኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራርና አባላት መጋቢት 24 የመጣውን ሁለንተናዊ ለውጥ ”’ ትናንት ፣ ዛሬና ነገን ለኢትዮጵያ ልዕልና፣” በሚል መሪ ሃሳብ የውይይት መድረክ ተዘጋጅቷል።
በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ለውጡን አስመልክቶ ለሁለቱም ምክር ቤት አመራሮችና አባላት ንግግር ያደረጉት የብልጽግና ምክር ቤት አባል እና የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በኢትዮጵያ ከመጋቢት 24/2010 ዓ.ም በፊት በርካታ የለውጥ ሙከራዎች ነበሩ ብለዋል።
ሙከራዎች የተደረጉ ቢሆንም የመጋቢት 24/2010 ዓ.ም በአይነቱ የተለየና የተሳካ ለውጥ መሆኑን በመጥቀስ ለውጡ ህዝባዊ፣ህገ መንግስታዊ እና ድርጅታዊ እንዲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የለውጥ ሮድማፕ በማዘጋጀት ለለውጡ ስኬት የተወጡት ሚና በታሪክ የሚወደስ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም መጋቢት 24 በኢትዮጵያ ህዝቦች የመጣው ለውጥ ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን ለኢትዮጵያና ለህዝቦችዋ አስገኝቷል ብለዋል።
ለውጡ ኢትዮጵያ ከመበታተን አደጋ የታዳገ ለውጥ መሆኑን አውስተዋል ። በተጨማሪም በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በፖለቲካዊ እና በዲፕሎማሲ የተገኙ ውጤቶች የኢትዮጵያን ከፍታ የጨመሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አያይዘውም ለውጡን ማስቀጠልና የህዝቦችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን ገልፀው፥ የሰላም ጠንቅ የሆኑ ጉዳዮችን በሠላማዊ ንግግርና ውይይት ብቻ መፍታት የስልጡነት መገለጫ በመሆኑ ብቸኛ አዋጭ መንገድ ነው ብለዋል።
የብልጽግና ምክር ቤት አባል እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው ለውጡ የኢትዮጵያን ህዝቦችን አንድነት ያጠናከረ፣ የህዝቦችን እኩል ተጠቃሚነትና የፖለቲካ ተሳትፎን ያረጋገጠ ቀን በመሆኑ እለቱን ልዩ ያደርገዋል ማለታቸውን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
ዘገባው የኢዜአ ነው












