::::::::::::::::::::::
በአገሩ ግሪክ ለኦሎምፒያኮስ የሚጫወተው ኮስቱላስ በዋናው ቡድን የመጫወት እድል የተሰጠው በዘንድሮው የውድድር አመት ነው።
ከ19 አመት በታች የዩኤፋ የክለቦች ዋንጫ ውድድር ላይ ለኦሎምፒያኮስ ታዳጊ ቡድን ባሳየው አቋም መነሻነት አሰልጣኝ ሆዜ ልዊዝ ሜንዴሊባር ወደ ዋናው ቡድን አሳድገውታል።
የ17 አመቱ ኮስቱላስ በዘንድሮው አመት ከተጠባባቂ ወንበር እየተነሳ በ 33 ጨዋታዎች 6 ግቦችን ሲያስቆጥር 3 የመጨረሻ ኳስ ማቀበል ችሏል።
በአውሮፓ እግር ኳስ 9 ቁጥር ጨራሽ አጥቂ መጥፋቱን ተከትሎ ታዳጊው በበርካታ ክለቦች ተፈላጊ ሆኗል። ተጫዋቹ ላይ ባላቸው ፍላጎት ገፍተው የመጡት ማንችስተር ዩናይትድ እና አርሰናል ተጫዋቹን እና ክለቡን ማነጋገራቸው ታውቋል።
ሁለቱም ክለቦች በፊት መስመራቸው ላይ የገጠማቸው ችግር ለመቅረፍ ግሪካዊውን አጥቂ የራሳቸው ለማድረግ እርስበርሳቸው ከሚያደርጉት ፉክክር በተጨማሪ ከቼልሲ፣ሪያል ማድሪድ፣ኤሲ ሚላን እና ዶርትሞንድ መገዳደር ይኖርባቸዋል።
በ- አልፈሪድ ነስሮ












