።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
የቀድሞ የማንቸስተር ሲቲ አማካይ በዌስትሚኒስተር ማጅስትራቴ ፍርድ ቤት የ12 ሳምንታት እስራት ተፈርዶበታል። ነገር ግን የአፋጣኝ የእስር ቅጣት መወሰን አስፈላጊ ባለመሆኑ ዉሳኔው ተፈጻሚ የሚሆነው በቀጣይ ሁለት ዓመታት ውስጥ ተመሳሳይ ጥፋት ከሰራ ብቻ እንደሆነ የእንግሊዝ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በኒውካስል ዩናይትድ እና ኩዊንስ ፓርክ ሬንጀርስ ክለቦች ጭምር ተጫውቶ ያሳለፈው የ42 አመቱ ባርተን በሰኔ 2021 በደቡብ ምዕራብ ለንደን በሚገኘው ቤታቸው በተፈጠረ ግጭት ሚስቱን ገፍቶ ከመሬት ላይ እንደጣላት ተነግሯል።
በድርጊቱ በግንባሯ ላይ እብጠት እና የአፍንጫ መድማት ጉዳት ደርሶባታል።

ጆይ ባርተን በበኩሉ በማጅስትራቴ ፍርድ ቤቱ ዉሳኔ በጣም ቅር እንደተሰኘ እና ይግባኝ ለማለት ማሰቡን ተናግሯል። ባርተን በእግር ኳስ ህይወቱ በሙሉ በሜዳ ላይ ሽኩቻዎች ይታወቃል።
በአካላዊ ግጭቶች እና ከተለያዩ ቡድኖች ተጫዋቾች ጋር የቃላት ልውውጥ በማድረግ ይታወሳል። በክህሎቱ እና አልፎ አልፎ በሜዳ ላይ በሚያሳየው ድንቅ ብቃቱ ቢደነቅም ከሜዳው ውጪ ያለው ባህሪው ስራውን ያጨልመው ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2007 የማንችስተር ሲቲ ቤት የቡድን አጋሩ ኦስማን ዳቦን ልምምድ ላይ እራሱን እስኪስት ድረስ በመደብደብ በተመሰረተበት ክስ ከእግር ኳስ ታግዶ ነበር። በ2005 የብላክበርን ሮቨርሱን አማካኝ ሞርተን ጋምስት ፔደርሰንን ሜዳ ውስጥ ሲጎሽም የሚያሳይ ቪዲዮ ወጥቶበት መነጋገሪያ እንደነበርም አይዘነጋም።
በ-ይበልጣል ሰውነት












