የ26 አመቱ የሊቨርፑል የቀኝ መስመር ተከላካይ የስፔኑን ክለብ በክረምት በነጻ ለመቀላቀል ፍቃደኝነቱን እንዳሳየ ተነግሯል።
ሪያል ማድሪድ ለተጫዋቹ የአምስት አመት ኮንትራት እንዳቀረበለትና ተጫዋቹ እንደተስማማ መገናኛ ብዙሐን ዘግበዋል።
የሪያል ማድሪድ ፕሬዚዳንት ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ክለቦች የሚገኙ ወሳኝ ተጫዋቾችን በነጻ የማስፈረም ውጤታማነት አላቸው።
አምና የአለም የተጫዋቾች የዝውውር ሂሳብን ያሻሽላል ይባል የነበረውን ምባፔን በነጻ ማስፈረማቸው ይታወሳል። በቀደሙት ዓመታትም ዴቪድ አላባን አና አንቶኒዮ ሩዲገርን በተመሳሳይ መንገድ ወደ ክለቡ ቀላቅለዋል።
ተረኛው አርኖልድ ካሳደገው የመርሲሳይዱ ክለብ በክረምት በነጻ የሚለቅ ሶስተኛው ተጫዋች ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ቀዮቹ በክረምት ሞሃመድ ሳላህን አና ቨርጅል ቫንዳይክን በተመሳሳይ በነጻ እንደሚያጡ ይጠበቃል።
ሪያል ማድሪድ በተጨማሪነት የክንፍ መስመር ወሳኝ ተጫዋቹ ቪኒ ጁኒየርን በሳኡዲ ክለቦች የሚቀማ ከሆነ ከአትሌቲክ ቢልባኦ ኒኮ ዊሊያምስን የማስፈረም እቅድ እንዳለው ተዘግቧል።












