48 ነጥብ 78 ኪሎሜትር የሚረዝመው የላሊበላ – ኩልመስክ – ሙጃ የአስፋልት ኮንክሪት የመንገድ ፕሮጀክት በግንባታ ሂደት ላይ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታወቀ።
በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ የዲዛይን ፣ የአፈር ጠረጋ ፣ የቆረጣ ፣ የሙሌት ፣ የውሃ ማፋሰሻ ቱቦ ቀበራ፣ የሰብ ቤዝ ሥራዎች እንዲሁም የድልድይ ግንባታ ጨምሮ እየተከናወነ መሆኑን ተቋሙ ገልጿል።
የመንገዱ አጠቃላይ የጎን ስፋት በገጠር ከ8-10 ሜትር ፣ በቀበሌ 16 ሜትር እንዲሁም በወረዳ 20.5ሜትር ስፋት ያለው ነው።
ለመንገዱ ግንባታ የሚውለው 1.8 ቢሊየን ብር በላይ ገደማ በኢትዮጵያ መንግስት ወጪ የተደረገ ነው ተብሏል፡፡
በአካባቢው በሚስተዋለው የፀጥታ ችግር ምክንያት አስፈላጊ የሆኑ የግንባታ ግብዓቶችን እና ማሽሪዎችን በበቂ ሁኔታ ለማማጓጓዝ የስራ ተቋራጩ መቸገሩ እንዲሁም በመንገዱ ክልል ውስጥ የተካተቱ ንብረቶች በወቅቱ አለመነሳት በግንባታው የሥራ ሂደት ላይ ተጽዕኖ አሳድረው ቆይተዋልም ብሏል ተቋሙ።
እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ የአትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከአካባቢው አስተዳደር እና ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ በማድረጉ አሁን ላይ የተሻለ የፕሮጀክት አፈፃፀም የተመዘገበ ሲሆን ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል።
መንገዱ ሲጠናቀቅ በዋናነት የላሊበላ ፣ የኩልመስክ እና የሙጃ ከተሞችን በቅርበት የሚያስተሳስር ሲሆን ወደ ላሊበላ ፍልፍል አብያተ-ክርስቲያናት መዳረሻ በመሆን ለቱሪስቶች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የሚያግዝ ይሆናል፡፡
በተጨማሪም በአካባቢው የሚመረቱትን የግብርና ውጤቶች ወደ ማዕከላዊ ገበያ በቀላሉ ለማድረስ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የአካባቢውን ማህበረሰብ የኢኮኖሚ እንቀስቃሴ እንደሚያፋጥን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር መረጃ ያመለክታል።
ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው ዓለም አቀፉ ቻይና ሲቪል ኢንጂነሪነግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ሲሆን የማማከሩንና የቁጥጥሩን ሥራ ቤዛ ኢንጅነሪንግ ኬኒያ ሊሚትድ እየሰራ ነው።












